በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ቀጣይነት ይኖራል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ ቀጣይነት ይኖራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የዝናብ ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ጋር ተያይዞ ወቅታዊ ዝናብ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋ እንደሚሄድ ገልጿል።
በዚህም በደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ገጽታ ይኖራቸዋል ብሏል።
በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎችን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል።
በተጨማሪም በውሃ አካላትና በአካባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በመነሳት በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብሏል።
አርሶ እና አርብቶ አደሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቁ መልካም ሁኔታዎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙና የግብርና ተኮር ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦችን መተግበር እንደሚገባ አስታውቋል።
ይህም ለበልግ ሰብሎች እና ቋሚ ተክሎች እድገት አዎንታዊ ሚና ያለው ሲሆን ለአፈር እርጥበት በመጨመር ለእርሻ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያለው።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ የሚጠበቀው ዝናብ የገጸ ምድር ውሃ ፍሰትን እንደሚያሻሽልም ጠቁሟል።