የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለመገንባት ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለመገንባት ትኩረት ተደርጓል
ባህርዳር ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፡- የመረጃ አያያዝ ስርአትን በማዘመን ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለመገንባት ትኩረት መደረጉን የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመተባበር በሰው ሃብት ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮረ የመረጃ ማረጋገጥ ስራ ላይ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሄዷል።
የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማርያም፤ በባህርዳር ከተማ በተካሔደው መድረክ ላይ እንደገለፁት፤ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ማረጋገጥ ዘርፉን ለማሳደግ ቁልፍ ተግባር ነው።
በተለይም የመንግስት ሰራተኛውን መረጃ በአግባቡ በመለየት፣ በማጥራትና በዘመናዊ መንገድ በማደራጀት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ እንደሚቻልም ነው ያመለከቱት።
ይህም የሰራተኛውን አቅም ለመገንባት፣ የደረጃ እድገት ሲሰጥና ጡረታ በሚወጣበት ወቅት የሚያጋጥመውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት እንደሚያስችል ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ሠራተኞችን መረጃ ማረጋገጥ እና የሰው ኃይል መረጃን የማዘመን ሥራዎችን ያካተተ ሪፎርም እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
ጥራት ያለው የመንግሥት አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ አሁን ያለውን የሰው ኃይል፣ ተቋም እና መዋቅር በዲጂታል ሥርዓት መረጃዎችን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ቢሮው የመረጃ አያያዝ ስርዓትን በማዘመን ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለመገንባት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ሰራተኛውን መረጃ ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
መረጃን ማጥራትና ዲጂታላይዝ ማድረጉ የመንግስት ሰራተኛውን አቅም ከመገንባት ባለፈ ጥቅማ ጥቅምን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተደራሽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የባህር ዳር አገልግሎት ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ ጤናው በበኩላቸው፤ ትክክለኛ እና ወቅታዊ የሲቪል ሰርቪስ መረጃን ማደራጀት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት የሠራተኞቻቸውን መረጃ በተሟላ መንገድ በመያዝ ለዲጂታል ሥርዓት ሽግግር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በአሁኑ ወቅትም በወረቀት የሚገኙ ፋይሎችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር እስከ ወረዳ ለሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።
የመድረኩ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ አገኘ እንዳሉት፤ የሲቪል ሰርቪሱን መረጃ በማጥራት ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተቀመጠው አቅጣጫ የሰራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ስልጠናው በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በኮምቦልቻና ደብረ ብርሃን ከተሞች መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።