ድምጻችን ዋጋ እንዳለው በመረዳት የምርጫ ካርድ ወስደናል - ኢዜአ አማርኛ
ድምጻችን ዋጋ እንዳለው በመረዳት የምርጫ ካርድ ወስደናል
ጅማ ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፡- ድምጻችን ዋጋ እንዳለው በመረዳት የምርጫ ካርድ ወስደናል ሲሉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ከተማ ነዋሪዎች ድምጻቸው ዋጋ እንዳለው በመረዳት በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሄኖክ ወርቁ፤ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና በተለይም አካል ጉዳተኞችን የሚያሳትፍ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሄኖክ አክለውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ወደ ምርጫ ጣቢያቸው በመሄድ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸው እስካሁን ያልወሰዱ ካሉ በቀሪ ቀናት እንዲወስዱም መክረዋል።
አቶ አብዶ አባጊዲ፤ ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ለሀገር ለውጥ የሚተጋ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
"ይህን ማሳካት የምችለው ድምፄ ዋጋ እንዳለው ተረድቼ ካርድ ስወስድ በመሆኑ ቀድሜ የምርጫ ካርድ ወስጃለሁ" ሲሉም አክለዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለመምረጥ ካርድ መውሰዷን የገለጸችው ወጣት ሀያት ጣሂር በበኩሏ፤ "የትምህርት ተቋማት ይበልጥ እንዲስፋፉ ስለምፈልግ፣ ይህን ፍላጎቴን የሚያሳካልኝን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች።
ወይዘሮ ፀጋነሽ ግዛውም እንዲሁ የምዝገባው ወቅት ሳይጠናቀቅ ቀድመው ካርድ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡም የምዝገባው ጊዜ ሳይጠናቀቅ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ ነዋሪዎቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።