ኢትዮጵያ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የልማት ትብብራቸውን የበለጠ ያጠናክራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የልማት ትብብራቸውን የበለጠ ያጠናክራሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የልማት ትብብራቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክሩ አስታወቁ፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ የ2026 የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዚዳንት ናኦኪ አንዶ ጋር ተወያይቷል፡፡
ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ከጃፓን ብሎም ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ጋር ላላት የረጅም ጊዜ ትብብር አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በመሠረተ ልማት፣ ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ በፋይናንስ፣ ቴክኒክ እና በአቅም ግንባታ ዘርፎች ላይ ኤጀንሲው እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጃይካ በአቪየሽን፤ በኀይል ልማት እና በመንገድ መሰረተ ልማተ ዘርፎች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ ለምታዘጋጀው የኮፕ 32 ጉባዔ እያደረገች ባለው ዝግጅት ላይም የተወያዩ ሲሆን ጃይካ በአየር ንብረት መቋቋምና አረንጓዴ ልማት እቅዶች ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ምክትል ፕሬዚዳንት ናኦኪ አንዶ በበኩላቸው፤ ጃይካ ለኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ የሚሰጠውን ድጋፍ እንደሚቀጥልና በተመሳሳይም ቅድሚያ በሚሰጣቸው መስኮች ላይ ትብብሩን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።