ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ያጠናክራሉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ገለጹ።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) እና ዓለም ባንክ የጸደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲኬላ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ተገልጿል።


 

በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ ላይ ያተኮረ እንደነበርም ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመደገፍ፣ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ይበልጥ ለማሻሻል፣ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚያስችሉ ስራዎች እና ቀጣይነት ባለው የኢኮኖሚ እድገት ግቦች ላይ በትብብር ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጥ መልኩ ትብብራቸውን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ማረጋገጣቸውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም