የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ ዲጂታላይዝ ማድረግ ፈጣን አገልግሎትን ለመስጠት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ ዲጂታላይዝ ማድረግ ፈጣን አገልግሎትን ለመስጠት ያስችላል
ደብረ ብርሃን/ኮምቦልቻ፤ሚያዝያ 12/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ ዲጂታላይዝ የማድረግ ተግባሩ ፈጣን አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ ⵆ
ቢሮው ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች የመረጃ ማረጋገጥ ሥራን የተመለከተ የምክክር መድረክ በደብረ ብርሃንና ኮምቦልቻ ከተሞች አካሄዷል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የአደረጃጀት ስራ ምዘናና ክፍያ ጥናት ዳይሬክተር አቶ አንተነህ ይስማው፤ በደብረ ብርሃን መድረክ እንደገለጹት የዲጂታላይዜሽን ትግበራው የሲቪል ሰርቪስ ግንባታን ለማፋጠን የሚያስችል ነው።
ይህም የመንግስት ሰራተኛውን በጠራ መረጃ ላይ በመመስረት መብትና ጥቅሙን በፍትሃዊነት በማሳደግ የስራ ተነሳሽነቱን ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ስርዓቱ ህግ አውጪና ህግ አስፈፃሚ አካላት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው እንዲወስኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ካሱ አበባው፤ በኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደው መድረክ ላይ እንደገለፁት፣ የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ በማጥራትና ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በክልሉ የሚገኙ ከ560 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞችን በመረጃ አያያዝ ስርዓት ወደ አንድ ቋት በማስገባት ፈጣንና ተደራሽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።
መረጃውን ዲጂታላይዝ የማድረግ ጥረቱ በአዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ መሰረት የሰራተኞችን መረጃ በማጥራት ፍትሃዊ የደሞዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትና ምደባ በመስጠት መብትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያስችላል ብለዋል።
በተጨማሪም ተጠያቂነት ያለው፣ ፈጣንና ፍትሃዊ አገልግሎት ለህብረተሰቡ በመስጠት የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረውም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኡስማን መሀመድ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ ከግንቦት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት የመንግስት ሰራተኞችን መረጃ የማጥራት ስራ ይሰራል።
በዚህም ለመረጃ ሰብሳቢዎችና ለባለድርሻ አካላት ስልጠና በመስጠት ግንዛቤ መፈጠሩን ጠቁመው፣ መረጃውን በጥንቃቄ በመያዝ ወደ ሲስተም ለማስገባትና ዲጂታል ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
ቆጠራው በስራ ላይ የሌሉ ሰራተኞችን ለመለየት፣ ከአንድ ተቋም በላይ የሚሰሩትንና የሰራተኞችን የትምህርት ደረጃ ለመለየት ለቀጣይ ስራ ዝግጁ ለማድረግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ በሪሁን ተገኝ በበኩላቸው፤መረጃ ለማጥራት የሚያስችሉ ባለሙያዎች ተለይተው ቴክኒካል ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
በከተሞቹ በተካሄዱ መድረኮችም ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከከተማና ከወረዳ የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።