የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን መሳብ ችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን መሳብ ችሏል
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን በማድረግና የግል ኢንቨስትመንትን ተሳትፎ በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገለጹ።
የአውሮፓ ሕብረት እና ኢትዮጵያ የቢዝነስ ፎረም " ዓለም አቀፍ የገበያ መግቢያ አቅምን መጠቀም" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዘላቂ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አድርጋለች።
ኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማድረግ ያላትን ዕምቅ አቅም መጠቀም የሚያስችል ለውጥ እያመጣች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ለማውጣት፣ ትብብርን ለመፍጠር፣ የገበያ አማራጮችን ለማሰስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ከሪፎርሙ በኋላ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ጨምሯል፤ የዋጋ ግሽበት ቀንሷል፤ ከወጭ ንግድ የሚገኘው የምንዛሪ መጠን በእጅጉ አድጓልም ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘገብ መተንበዩን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በመተግበር ምቹ ለኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን እያጠናከረች መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና የዲጂታል ግብይትን ማጠናከር የሚያስችል የዲጂታል ክፍያና አገልግሎት ስርዓት ማዘመኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በብዝሀ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተመራጭ መሆኗን በመጥቀስ፣ የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በታዳሽ ሀይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ጋርመንትና መሰል ዘርፎች መሰማራት ይችላሉ ብለዋል።
ለኢንቨስትመንት ምቹ ሥነ ምህዳርና መሰረተ ልማት በመዘርጋት ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረትና አባል ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሚችሉ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንቨስተሮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጆዜፍ ሲከላ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መስራች፣ የቡና መገኛ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነች ታሪካዊ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያጠናክሩ የፖሊሲ እርምጃዎችን በመውሰድ መዳረሻው የት እንደሆነ በግልጽ አሳይታለች ብለዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማትና የዲጂታል መሰረተ ልማት ይፈልጋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ሕብረቱ በገጠር መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት እና ኢትዮጵያ ቢዝነስ ፎረም በንግድ ድርጅቶች መካከል፣ በመንግሥት እና በንግድ ድርጅቶች መካከል ገንቢ ውይይት ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሀፊ ዋምኬሌ ሜኔ፤ በአፍሪካ አሕጉር ከአራት ሺህ ላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች በመሳተፍ በዓለም ቀዳሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ትብብር በአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የተበጣጠሰ የእሴት ሰንሰለት ባለው የዓለም ገበያ በአፍሪካ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ የቢዝነስ ስራዎችን የሚያቀላጥፉ የጉምሩክና የፋይናንስ ስርዓቷን እያዘመነች መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትርጉም ያለው ሪፎርም በማድረግ ሀገሪቱን በአፍሪካ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት አድርጓታል ብለዋል።
በዚህም ንግድና ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን በላይ የአፍሪካ ሕዝብ መነቃቃት የሚፈጥር የገበያ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።