ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው

ሐረር ፤ሚያዚያ 12/2018 (ኢዜአ) ፡-በሐረሪ ክልል በስፖርት ዘርፍ በሚከናወኑ ስራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት  ምቹ ሁኔታ እየተፈጠሩ መሆኑን የስፖርት ቤተሰቦች ገለጹ።

በክልሉ ‎የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማትና  የፕሮጀክት ስልጠናዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑ ተመላክቷል ።


 

በክልሉ የሐረር ጀጎል እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ አክረም መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጸው በክልሉ ከዚህ ቀደም ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራትና የድጋፍና እገዛ  ተግባራት ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት ህፃናትና ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁሞ ለዘርፉ ስልጠና የተሰጠው ትኩረት አሰልጣኞችንም እያበረታታ መሆኑን አመልክቷል ።

በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታና የድጋፍ ስራዎች  ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን ወደ ስፖርቱ ለመምጣት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው ያሉት ደግሞ የታዳጊ ፕሮጀክት እግር ኳስ አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ፈይሰል መሀመድ ናቸው።


 

በተለይ ቀደም ሲል እንደ ችግር ሆኖ ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ ተቀራርቦ የመስራት ተግዳሮቶችን ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የቅንጅት ስራዎች እየጎለበቱ በመሆኑ ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ተግባራትን  አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አመላክተዋል።

የታዳጊ ፕሮጀክት ሰልጣኝ የሆነው ማስተዋል ታጠቅ በበኩሉ “በከተማው ከኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር በየአካባቢው የተከናወኑ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች ተሰጧችንን ለማውጣት እድል እየፈጠሩልን ነው ብሏል።

በተለይ በታዳጊዎች ፕሮጀክት ታቅፈን የሚሰጠን ስልጠና ወደፊት ታላላቅ ክለቦች ላይ መሳተፍ የሚያስችለን ክህሎት እየወሰድን እንገኛለን ፤ እኛም ደግሞ  በተገቢው መንገድ እየሰራን እንገኛለን ሲል ገልጿል። 


 

በክልሉ ለታዳጊ ፕሮጀክት ስልጠና እየተደረገ የሚገኘው ድጋፍና በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ግንባታ ተስፋ የሚሰጡ ስራዎች ሆነው አግኝተናቸዋል ያለው ሌላው የታዳጊ ፕሮጀክት ሰልጣኝ አብረሃም አሸናፊ ነው።

እኛም የነገዋ ኢትዮጵያ የምትጠብቅብንን አሸናፊነት ለማምጣት ከወዲሁ ተግተን እየሰራን እንገኛለን ብሏል

የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙራድ አብዲ በበኩላቸው በክልሉ ‎የስፖርት ማዘውተሪያ ስራዎችን የማልማትና ፋሲሊቲዎችን በማሟላት  ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ተግባራት  በትኩረት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።


 

በዚህም የክልሉ መንግስት ቀደም ሲል የነበሩ የማዘውተርያ ስፍራዎችን የማዘመን እንዲሁም በየወረዳው አንድ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ የመገንባት ስራ በእቅድ ይዞ እያከናወነ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

እግር ኳስን ጨምሮ በሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ክልሉን ብሎም ሀገርን ወክለው በዓለም አቀፍ መድረክ የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ማፍራት የሚያስችሉ የታዳጊ ፕሮጀክት ስልጠናዎች አዲስ ፎርማት ተቀርጾላቸው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም