የዲጂታል አሰራርን በማዘመን የመረጃ ማረጋገጥና ማደራጀት ተግባር ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል አሰራርን በማዘመን የመረጃ ማረጋገጥና ማደራጀት ተግባር ይጠናከራል
ሰመራ፣ሚያዚያ 12/2018(ኢዜአ)፡- የዲጂታል አሰራርን በማዘመን መረጃን የማረጋገጥና የማደራጀት ተግባር እንደሚጠናከር የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች የመረጃ ማረጋገጥ ስራን የተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሰመራ እየተካሄደ ነው።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩም የአፋር ክልል፣ የዞንና የወረዳ የሰው ሃብት ዳይሬክተሮች እየተሳተፉ መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) እንዳሉት በዚህ ወቅት የዲጂታል አሰራርን መተግበር አስፈላጊ ነው።
በዚህም የዲጂታል አሰራርን በማዘመንና የሲቪል ሰርቫንቱን መረጃ የማረጋገጥና የማደራጀት ተግባር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን እውን ማድረግ ያለው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ገልፀው በተደራጁና ዘመኑን ባገናዘቡ መረጃዎች የተሳለጠ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማስፈን ላይ በፍጥነት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ የሰራተኛውን መረጃ ከዲጂታል መታወቂያ ጋር የማያያዝ ሰራ ተግባራዊ ማድረጉ እንደ አገር የተጀመረውን መረጃን የማዘመንና ዕውን የማድረግ ተግባርን የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።
በዚህም መረጃን በማዘመን ስልጡን የሆነ አገልጋይ ሲቪል ሰርቫንትን ማጠናከር ላይ ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን እውን በማድረግ ረገድ እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ይህም የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ አገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩም የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የሰው ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል።