በምስራቅ ጎጃም ዞን በአረንጓዴ አሻራው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አገር በቀል ችግኞች ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በአረንጓዴ አሻራው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አገር በቀል ችግኞች ተዘጋጅተዋል
ደብረ ማርቆስ፤ሚያዚያ 12/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው አገር በቀል ችግኞች በስፋት መዘጋጀታቸውን የምስራቅ ጎጃም ዞን የተፈጥሮ ሃብት መምሪያ አስታወቀ።
በአረንጓዴ አሻራው የሚተከሉት ችግኞችም የተለያዩ ዝርያ ያላቸው መሆኑን በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ አቶ ንጉሴ ሽመልስ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት በአረንጓዴ አሻራና በመደበኛው የክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ52 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን የተራቆተ መሬት ላይ ችግኞች እንደሚተከሉም ነው ያስረዱት።
ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥም የኮሶ፣ የግራር፣ የወይራ፣ የጌሾ፣ የዋንዛ፣ የባህር ዛፍ፣ የሳስቫኒያ፣ የዲክረንስ፣ የፈረንጅ ጽድና ሌሎች የችግኝ ዓይነቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ችግኞቹን ማዘጋጀት የተቻለውም ከ38 ሺህ በላይ በሚሆኑ የመንግስት፣ የማህበራትና የግል ችግኝ ጣቢያዎች መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
እንደ መምሪያው ገለጻ፥ በበጀት ዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ ከ261 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ ተከናውኗል።