የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመረጃ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተገልጋይ እርካታን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመረጃ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተገልጋይ እርካታን እያሳደገ ነው
ጅማ፤ ሚያዚያ 12/2018(ኢዜአ)፡-የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመረጃ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተገልጋይን እርካታ ማሳደጉ ተገለጸ።
"ዲጂታል ኢትዮጵያ" ተግባራዊ እያደረጉ ካሉ የመንግስት ተቋማት መካከል አንዱ የፍትህ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህ ረገድ የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመረጃ አያያዙንና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ጭምር ችሎት የሚከታተሉበትን አሰራርን እየተገበረ ይገኛል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ የጅማ ዞን ከፍተኛ የፍርድ ቤት ተገልጋዮችና ፕሬዚዳንቱን አነጋግሯል።
ከፍርድ ቤቱ ተገልጋዮች መካከል በጅማ ዞን ማና ወረዳ ነዋሪ አቶ ጀዋር አባራያ የፍትህ ሂደቱን ለመከታተል የቪዲዮ ኮንፈረንስና ዲጂታል አሰራሮች መተግበራቸው ፍትህ ለማግኘት እስከ ጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ በመጓዝ ያወጡት የነበረውን ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።
በዞኑ የነዲ ጊቤ ወረዳ ነዋሪ ሚስባሂ ሼህ ኢማም በበኩላቸው እንዳሉት የፍርድ ቤቱ ዲጂታላይዝድ አገልግሎት አሰጣጥ ከመደበኛ ሥራቸው ሳይነጠሉ ባሉበት ሆነው ፈጣን ፍትህ ለማግኘት አስችሏቸዋል።
የፍርድ ቤቱ ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ መረጃዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት የሚያስችልና ሥራን የሚያሳልጥ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የህግ ባለሙያ እና ጠበቃ ታደለች ዲባዩ ናቸው።
የፍትህ አገልግሎቱ ዲጂታላይዝድ መደረግ ለተገልጋዩም ሆነ ለህግ ባለሞያዎች እፎይታ ሰጥቷል ብለዋል።
"በወረዳ ላይ ላልተፈቱ ችግሮች ተገልጋዮች ወደ ጅማ ከተማ መምጣት አይጠበቅባቸውም" ያሉት ደግሞ የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ታጁ ሸሪፍ ናቸው።
ዘመናዊ አሰራሩ ተገልጋዮች አቤቱታቸውን በኢ-ፋይል ልከው ባሉበት ቀርበው የመከራከር ወይም ጉዳያቸውን የመከታተል እድልን ያሰፋ ነው ብለዋል።
አገልግሎቱ ከወረቀት ንክኪ በጸዳ መልኩ መሰጠቱ አገልግሎቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ የመረጃ ግልጽነትን ለመፍጠር ማገዙን ጠቁመዋል።
የጅማ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቶፊቅ ሸምሱ በበኩላቸው፣ ዞኑ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ተደራሽነትን እውን ለማድረግ የተለያዩ መተግበሪያዎች መበልጸጋቸውን ገልጸዋል።
ችሎቶች ጥራቱን በጠበቀ የቪዲዮ ኮንፈረንስ እየተካሄዱ መሆናቸውን ጠቅሰው ለክስ፣ ለይግባኝና መሰል አገልግሎቶች ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መምጣት ሳያስፈልግ በወረዳ እና በክላስተር ቀበሌዎች ሆነው መከታተል እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዞኑ 19 ወረዳዎች በዐቃቤ ህግ እና በፍርድ ቤት መካከል የወረቀት ንክኪ ሳይኖር በዲጂታል መንገድ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም የፍትህ ስርዓቱን የሚያሳልጡ አገልግሎቶችን በሁሉም ወረዳዎች በማዳረስ "ዲጂታል ኢትዮጵያን" እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።