በምስራቅ ቦረና እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም የችግኝ ተከላ እየተከናወነ ነው
ነገሌ ቦረና፤ ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ፡- በምስራቅ ቦረና ዞን እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተከላ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ አልዬ አረባ ፤በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከ32 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለማፍላት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።
እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ድርቅንና የአካባቢ መራቆትን በመቋቋም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያስገኙ ከ25 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለማዘጋጀት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል የደን ዛፍ፣ የተለያዩ ፍራፍሬዎች እና የእንስሳት መኖ የሚሆኑት ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የተዘጋጁት ችግኞች በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ድረስ የሚጥለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም የሚተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።
እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀምም እስካሁን በ 2 ሺህ 83 ሄክታር መሬት ላይ ችግኞች መተከላቸውንም ነው ያስታወቁት።
በችግኝ ተከላው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተራቆተ ከ7 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በመከለል ለማልማት ትኩረት መሰጠቱን አመላክተዋል።
በዘላቂ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ ከ159 ሺህ በላይ ህዝብ እየተሳተፈ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዞኑ እየተስፋፋ የመጣው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ የሚከሰተውን ድርቅና የአካባቢ መራቆት ለመከላከልና ለመቋቋም ማስቻሉን አክለዋል።
መርሃ ግብሩ ለዞኑ ህዝብ መሰረታዊ ችግር የነበረውን የመጠጥ ውሀና የእንስሳት መኖ እጥረት እያቃለለ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
በዚህም በየዓመቱ ለዞኑ ህዝብ ከመንግሥት ሲቀርብ የነበረው የመጠጥ ውሀና የእንስሳት መኖ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት ማስቻሉን አብራርተዋል።
በዝናብ አጠርና ቆላማ ወረዳዎች የተጀመሩት የበጋ መስኖ፣ የተፋስስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ሁለንተናዊ እገዛ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።