ቀጥታ፡

አሜሪካ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ቁርጠኝነቷን ገለጸች

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 12/2018 (ኢዜአ)፦አሜሪካ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትራስፎርሜሽን የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን፣በዋሺንግተን ዲሲ ከተካሄደው የዓለም ባንክ እና የአይኤምኤፍ (IMF) የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን፣ከከፍተኛ የአሜሪካ የግምጃ ቤት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት ጋር በኢኮኖሚያዊ ትብብር ዙሪያ ተወያይቷል።

ውይይቱ በዋነኝነት ያተኮረው የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነቶችን በማሳደግ ላይ ሲሆን፣ በተለይም እንደ አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ያሉ ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የኢኮኖሚ ሪፎርም አበረታች ሂደት አድንቀዋል።

ባለሥልጣናቱ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን የምታደርገውን ድጋፍ በቴክኒክ ድጋፍ፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደምታጠናክርም በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሁለቱም ወገኖች ቅድሚያ በሚሰጧቸው የጋራ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ወደፊት ለማራመድ፣ ዕድገትን ለማፋጠን እና የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትስስር ለማስፋት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም