የኢትዮጵያ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለአፍሪካ አርአያ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለአፍሪካ አርአያ ናቸው
አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ለቀሪዎቹ አፍሪካ ሀገራት ትልቅ ተምሳሌት ያለው በመሆኑ ተሞክሮውን ሊቀስሙ ይገባል ሲሉ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አትሌቶች ገለጹ።
በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የ2026 ዓለም አቀፍ የአንድ ቀን የግራንድ ፕሪክስ ውድድር ላይ የተሳተፉ ስመ ጥር አትሌቶች፣ በከተማዋ የተገነቡ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
አትሌቶቹ የዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ የአዲስ ስፖርት ፓርክን እና የወንዝ ዳርቻ ልማትን ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፤ በተገነቡት መሠረተ ልማቶች ጥራትና ውበት መደነቃቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ያስታወሱት አትሌቶቹ፣ በታሪካዊቷ ከተማ አዲስ አበባ በመገኘታቸው ላቅ ያለ ኩራት እንደተሰማቸው በአጽንኦት ገልጸዋል።
የዚምባብዌ አትሌት አሽሊ ቲናሼ ሚለር፤ የታላላቅ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው ኢትዮጵያ፣ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት እጅግ የሚያስደስት እና ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ተናግራለች።
የቦትስዋናው አትሌት ሌትልሆጎኖሎ ሞክጌቲ ፤የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ ዘመናዊና የተሟላ ግብዓት ያላቸው መሆናቸው ቀልቡን እንደሳበው በመግለጽ፣ እንዲህ ያሉ መሰረተ ልማቶች የአፍሪካ አትሌቶች በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝ እንደሆኑ ተናግሯል።
የሴኔጋል አትሌት ሩጊ ሶው፤ በኢትዮጵያ የታዩት የስፖርት መሠረተ ልማቶች ዘመናዊና አቅምን የሚያሳድጉ በመሆናቸው፣ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በሞዴልነት ሊወሰዱ እንደሚችሉ አስረድታለች።
የኬንያ አትሌት ፓሊን ሙርጋ፤ እንዲህ ያሉ ድንቅ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በየስፍራው ሊገነቡ እንደሚገባ አመልክታ በዚህም የሀገርን ገጽታ በስፖርት መገንባት እንደሚቻል ገልጻለች።
በአጠቃላይ አትሌቶቹ፣ በከተማ ልማትና በስፖርት መሠረተ ልማት ረገድ ኢትዮጵያ እያሳየችው ያለው ፈጣን ለውጥ ለቀጣዩ የአፍሪካ ትውልድ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም በአዲስ ስፖርት ፓርክ ውስጥ ሀውልት የቆመላቸውን ታዋቂ አትሌቶች በመመልከት ወጣቱ ትውልድ "እኔስ መቼ ነው የሀገሬን ስም በዓለም አደባባይ የማስጠራው" የሚል በጎ የቁጭት ስሜት እንዲያድርበትና ለላቀ ስኬት እንዲነሳሳ የሚያደርግ መሆኑም አትሌቶቹ ተናግረዋል።