ቀጥታ፡

መንግሥት የጠራ ፖሊሲ ሲኖረው ፍሬያማ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ያሳያሉ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- መንግሥት የጠራ ፖሊሲ ሲኖረውና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂው ያን ለመመገብ የሚያስችል ሲሆን ምን ዓይነት ፍሬያማ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል የተጀመሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ያመላክታሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ የሐሮ ደንዲ ሎጅን የመረቁ ሲሆን፤ ከምረቃው በኋላም ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

በማብራሪያቸውም፤መንግሥት የጠራ ፖሊሲ ሲኖረው፣ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂው ያን ለመመገብ የሚያስችል ሲሆን እና የማስፈጸም ዐቅም በተቋም ደረጃ እየገነባ ሲሄድ ምን ዓይነት ፍሬያማ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ያመላክታሉ ብለዋል።

እንደ ሀገር አምሥት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ ብለን የለየናቸው ሴክተሮችን ብንመለከት፤ ከፖሊሲ፣ከስትራቴጂ እና ከአፈጻጸም አንጻር ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ ይገኛሉ ሲሉም አብራርተዋል።

ለአብነትም ከኢንዱስትሪ አንጻር፤ ቀደም ሲል መንግሥት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ይገነባ እንደነበር አውስተው አሁን ግን የኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት የሚችሉ የግል ሴክተሮች መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።

በርካታ ፋብሪካዎች፣ ኢንዱስትሪል ፓርኮች፣ ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች መሥራት ስንጀምርም፤ ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት ወደ ውጭ የምንልከውን ቁጥርም ለማሳደግ በእጅጉ አግዘዋል ነው ያሉት።


 

ከግብርና አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ግብርና በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት አውስተው፤ በሚሊዮን የሚቆጠር አርሶ አደርን በክላስተር በማደራጀት ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ ፓምፕና የተለያዩ ማሽነሪዎችን ማቅረብ ስንችል አነስተኛ አርሶ አደሮች በሚያርሷቸው ማሳዎች ጭምር የሚገኘው ምርት አድጓል ብለዋል።

የግል ሴክተሩም በዚያው ልክ ኢንቨስት ማድረግ እየጀመረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። ለምሳሌ ቡናን ብንመለከት፤100 ሺህ ሔክታር ገደማ መሬት የግል ሴክተሩ ወስዷል፤ ይህን በመስኖ ከሠሩ የምናመርተውን ግማሽ ያህል ሊያመርቱ ይችላሉ ነው ያሉት።

በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን በመግለጽ፤ይህም በፍጆታችን ብቻ ሳይሆን በኤክስፖርታችን የሚታይ ሆኗል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በማዕድን ዘርፍም፤ቀደም ሲል በዘርፉ ሊጠቀስ የሚችል ሥራ አለ ለማለት እንደሚከብድ በመጠቆም፤ ኤክስፖርቱም ውስን እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ግን በወርቅ፣ በማዳበሪያ፣ በጋዝ፣ በሴራሚክ፣ በሲሚንቶ ዘርፎች መንግሥት ዐይን ሲገልጥና ሲያመቻች የግል ሴክተሩ ተሳትፎ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ውጤቱ ያሳያል ብለዋል።

የማዕድን ሴክተሩ ፖሊሲ ላይ ባስቀመጥነው ልክ ውጤቱ በኤክስፖርት ውጤታችን ጭምር እየታየ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከቴክኖሎጂ አንጻርም፤ እየተሠራ ያለው ሥራ ሞባይል ማስፋት፣ ዳታ ማስፋት ብቻ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

ስለሆነም በቴሌኮም ብቻ የነበረውን ሌላ ተቋም (ሳፋሪኮም) ስናመጣ ውድድር ሲጀመር፣ ኤ አይ ሲጨመር፣ መሶብ ሲታከል፣ 5 ሚሊየን ኮደሮች ሲጨመር ዘርፉ ኢኮኖሚያችንን የሚያነቃቃና የሚያስተሳስር እየሆነ መጥቷል ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

ከቱሪዝም አንጻርም ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክና ባህል ማሳየት የሚያስችል መሠረተ-ልማት እንዳልነበረ አንስተዋል። ይህን እንቀይር የሚል እሳቤ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም በመግለጽ።


 

በዚህም መሠረት፤በገበታ ለሸገር፣በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ ባለሃብት አስተባብረን የሠራናቸው ሥራዎች፤የቱሪዝም ሴክተሩን አስተምረን ዐይን ገልጠን ወደ ግል ሴክተር እንዲገባ ማድረግ አለብን የሚል ነበር ብለዋል።

በዚህም በርካታ ቦታዎች በገበታ ኢንሼቲቭ መሠራታቸውን እና በዚያው ልክ የግል ሴክተሩ መግባቱን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ለኮፕ 32 ስንወያይም አሁን 20 ሺህ ገደማ ያለው ለእንግዶች የሚሆን የአልጋ ዐቅማችንን ወደ 80 ሺህ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሠሩ መሆኑን አይተናል፤ይህም ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

በዚህ ላይ ኤርፖርቱ፣ኢነርጂው፣ መንገዱ እየተጨማመረ እየመገበው ሲሄድ፤ አጠቃላይ ፖሊሲውን በከፍተኛ ደረጃ አጉልቶ ያሳያል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም