የዋንጫውን መዳረሻ ይወስናል በተባለው ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ አርሰናልን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የዋንጫውን መዳረሻ ይወስናል በተባለው ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ አርሰናልን አሸነፈ
አዲስ አበባ ፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ ግብር ማንችስተር ሲቲ አርሰናልን 2 ለ 1አሸንፏል።
ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ራያን ቸርኪ እና አርሊንግ ሃላንድ ለውሃ ሰማያዊዎቹ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ካይ ሃቫርትዝ ለአርሰናል ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ማንችስተር ሲቲ የተሻለ ብልጫ ነበረው።
አርሰናል በጨዋታው ያገኛቸውን ግልጽ የግብ እድሎች አልተጠቀመም።
በሊጉ 20ኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ሲቲ በ67 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከሊጉ መሪ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ አድርጓል።
በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርሰናል በ70 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የዛሬው ውጤት በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለውን የዋንጫ ፉክክር ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።
ዛሬ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች በመርሲሳይድ ደርቢ ሊቨርፑል ኤቨርተንን 2 ለ 1 አሸንፏል።
አስቶንቪላ ሰንደርላንድን 4 ለ 3፣ ኖቲንግሃም ፎረስት በርንሌይን 4 ለ 1 አሸንፈዋል።
የ33ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገ ክሪስታል ፓላስ ከዌስትሃም ዩናይትድ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።