የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
ክልሎች፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በሀገራችን ሁሉም ክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
የንፋስ ሃይል
በቀጥታ የምናመራው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ ኢተያ አካባቢ ነው። በኢተያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተገኝተው የመረቁትን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫን እንመለከታለን።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 100 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ልማት ወደ ፊት እየተራመደች መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ሥራ ነው። ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከጉባ እስከ አሰላ፣ ገናሌ እና አይሻ በሃይል ልማት ዘርፍ ትልቅ ትርጉም ያላቸውን ፕሮጀክቶች አስመርቃለች። የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ደግሞ በዚህ ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምርቃቱ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ከለውጡ በፊት የነበረው 4 ሺህ ሜጋ ዋት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም አሁን ላይ ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት በመድረስ ከእጥፍ በላይ እድገት የተመዘገበበትን ትልቅ ስኬት አንስተዋል።
የስንዴና ገብስ ሰብሎችን በከፍተኛ መጠን የሚያመርተው አርሲና አካባቢው አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚመረትበት አካባቢ መሆኑንም ገልጸዋል። በመሆኑም በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እናስቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
ቢሾፍቱ
የኦሮሚያ ክልል መንግስት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማም በዚህ ሳምንት በቢሾፍቱ ሀርሰዴ አዳራሽ መካሄዱ ይታወቃል። በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ ስኬታማ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል። በተለይም የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተሻለ መልኩ ያሳደጉ የከተማ እና የገጠር የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ነው ያስረዱት።
ከዚህ ባለፈ የክልሉን የልማት ሥራዎች ለማቀላጠፍ የሚያግዙ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የአገልግሎት አሰጣጥ አሰራሮች መተግበራቸውንም ተናግረዋል። የቢሾፍቱ መድረክ በድምሩ የግብርና፣ የገጠርና የከተሞች ልማት፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ክንውን በዝርዝር የታየበት ውጤታማ መድረክ እንደነበረም ተመላክቷል።
የአሎማ ክላስተር
ሌላ የሳምንቱ ዓበይት ጉዳይ ወደ አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ይወስደናል። የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በዚህ ሳምንት ነው። በመስኖ የለማ የስንዴ ክላስተር የተጎበኘበትና በተሁለደሬ ወረዳ በክላስተር ለሚከናወነው የተቀናጀ የፍራፍሬ ልማት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ የተጀመረበት እንዲሁም የክልሉ የ10 ዓመት የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ይፋ የተደረገበትን ሁነት እናገኛለን።
በእነዚህ ሁነቶች ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የመደመር መንግሥት በሁሉም ዘርፎች ለሀገር እድገትና ማንሰራራት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም በግብርና፣ በመስኖ ልማት፣ በቱሪዝምና ሌሎች መስኮች በተግባር የተመለከትናቸው የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የአሎማ ክላስተር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የሓይቅ ዳር አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን የማቻል ጥረት በስኬት መንገድ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገርን የማሻገር ሥራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የታሪክ መሰነጃ
የሳምንቱ በረራችን እንደቀጠለ ሲሆን አሁን ደግሞ የሰው ልጅ መገኛ፣ የኤርታሌ ትኩሳት የሚገነፍልባትና የአዋሽ ወንዝ የተንጣለለባት አፋር ክልል ገብተናል።
በአፋር ቆይታችን ትኩረታችንን ሰመራ በማድረግ በስፍራው ሊገነባ የታሰበውን የሉሲ ሙዚየም እንመለከታለን። ሙዚየሙን ለመገንባት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የአፋር ክልል ቱሪዝም ቢሮ የፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት አድርገዋል። ለሉሲ አፋር ቤቷ ነው፤ ሀዳር የተባለው ስፍራ ደግሞ መገኛዋ ነው። በመሆኑም በዚህ ከሰው ልጅ መገኛ ጋር የተቆራኘን ስፍራ ሙዚየም ገንብቶ፣ የቱሪስት መስህብ አልምቶና አካባቢውን በስፋት አስተዋውቆ የገቢ ምንጭ ማድረግ ሲቻል ለምን ተዘንግቶ ቆየ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ይሆናል። የጊዜ ጉዳይ ሆኖ አሁን አፋር ሰመራ ላይ በሉሲ የተሰየመ የሀገር ታሪክና ቅርስ ማጣቀሻ፤ የአፋር ክልል ህዝብ ቱባ ባህሎች ማሳያ የሆነ ሙዚየም ለመገንባት ዝግጅት መደረጉ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ የሚገነባው ሙዚየም የሀገር ታሪክና ቅርስ የሚሰነድበት፣ የአፋር ክልል ህዝብ ቱባ ባህሎች ተጠብቀው የሚዘልቁበት፣ የሰው ልጅ አመጣጥና ዝግመተ ለውጥ የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ የሚካሄድበት ይሆናል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት የሙዚየሙ ግንባታ በ18 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገለግሎት የሚበቃ ይሆናል። የአፋር ክልል በመስኖ ቢያለሙበት፣ የጥጥ እና የቴምር ልማት ቢካሄድበት ተዝቆ የማያልቅ እምቅ አቅም ያለው መሆኑን አንስተዋል። በመሆኑም በለውጡ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን እምቅ የቱሪዝም ሃብቱንም በማልማትና በመጠበቅ የሃገር ሃብት የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የሉሲ ሙዚየም ግንባታ ሁነኛ ማሳያ ነው።
የሳምንቱ ቅኝታችን እንደቀጠለ ሲሆን አሁን ደግሞ በቀጥታ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ተገኝተናል። አሶሳ በሳምንቱ በሃይማኖት አባቶች ጸሎትና ዱአ ተባርካ ስለ ሰላምና አብሮነት የሚመከርባት ከተማ ሆና እንግዶቿን ተቀብላ አስተናግዳለች።
የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ምሁራንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት 7ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ "ሰላምን ይበልጥ ለማስፋት እና ለማስረጽ የሃይማኖቶች ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ አባቶች ስለ ሰላም እና አብሮነት እንትጋ ለትውልድ ግንባታም መስራት ግድ ይለናል በማለት አፅንኦት በመስጠት መክረዋል።
የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኃይማኖቶች ለሰላም እና ለህዝቦች አብሮነት ያላቸውን አስተምህሮ በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ሀገራዊ የልማት ስራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብለዋል። በኢትዮጵያ ሰላምን ለማጽናት እና የወንድማማችነት ድልድይን ለመገንባት እንስራ በማለትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከአሶሳ ወደ ሀዋሳ
ከአሶሳ ወደ ሀዋሳ ስንጓዝ የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ-AGRA) ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የኤልቶ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን የሥራ እንቅስቃሴን መጎብኘታቸውን እናገኛለን። በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጥምረቱ የቦርድ ሊቀ መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ አርሶ አደሮች ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት ጥሩ ተስፋ የተሰነቀበት መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል። የግብርና ልማትን የማዘመን፣ ምርታማነትን የማሳደግና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የጥምረቱ ፕሬዚዳንት አሊስ ሩህዌዛ፤ በአፍሪካ የግብርና ስርዓት ሽግግርን ለማጠናከር በተለይም አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል። በአፍሪካ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ሂደት ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ለውጥ አስደናቂ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ሌሎች
በዚህ ሳምንት በሁሉም ክልሎች ባደረግነው ምልክታ በተለይም የምርጫ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ዜጎች የምርጫ ካርዳቸውን እየወሰዱ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምረጡኝ ቅስቃሳ ማድርጋቸውን ቀጥለዋል። የግብርና ልማት ስራዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅት እና ሌሎችም የልማት ሥራዎች በተጠናከረ መልኩ የቀጠሉበት ሳምንት ነበር ማለት ይቻላል።