ለሀገራዊ ምክክሩና ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ሚናችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩና ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ሚናችንን እንወጣለን
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩን እና መጪውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ ለማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የፓርቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮች ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን አቋምና ለምርጫው እያደረጉት ስላለው ዝግጅት አብራርተዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኦሮሚያ የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ ያለው ተግባር ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረት የሚሆን ነው ብለዋል።
የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን በስምንት ወራት መራዘሙም ኃላፊነቱን በብቃት ለመወጣት እንደሚያስችለው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው፣ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን የወል ሐሳቦች ላይ መግባባት የሚፈጥሩበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሂደቱን በታላቅ ተስፋ እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ዋና ጸሐፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ኢዜማ በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ላይ ንቁና ጠንካራ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት ለስኬታማነቱ ሚናቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመራሮቹ ጠቅሰዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የኦሮሚያ የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ፥ የሚዲያ ተቋማት ለፓርቲዎች የክርክር መድረክና በቂ የአየር ሰዓት መመደባቸው ለዴሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ተናግረዋል።
በእጩዎች ላይ የሚደርስ ጫና አለመኖሩና ሂደቱ ሰላማዊ መሆኑ የምርጫውን ተአማኒነት እንደሚያሳድገው የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ናቸው።
መንግሥት ለፓርቲዎች እያደረገ ያለው ድጋፍና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መጠናከሩ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ስኬታማነት የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የኢዜማ ዋና ጸሐፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲያቸው በርካታ እጩዎችን በማስመዝገብ ጠንካራ ፉክክር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አመራሮቹ ሕዝቡ በቀሪ ቀናት የምርጫ ካርድ በመውሰድ መብቱን እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል።
ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም በተቃራኒ መቆም የሕሊናም የታሪክም እዳ መሆኑን ጠቅሰው፥ በሀገር ሉዓላዊነትና በጋራ ጥቅም ጉዳዮች ላይ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን እንደሚያስቀድሙ በአፅንኦት ጠቅሰዋል።