ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው
ሀዋሳ ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ከተማዋ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የሲዳማ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ተናገሩ።
የከተማዋ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ማጠናቀቂያ የምስጋናና ዕውቅና እንዲሁም የአራተኛ ዙር የኮሪደር ልማትና የሐይቅ ዳርቻ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሄዷል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይም የሲዳማ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል በማድረግ ከተማዋ አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ እንድትሆን ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ተጠናቀው ለአገልግሎት በበቁ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎች የተሳተፉ አመራርና ባለሙያዎችን፣ የሥራ ተቋራጮችን እና በተለያየ መንገድ አስተዋፅኦ ያደረጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን አመስግነዋል፡፡
ባለፉት የኮሪደር ልማት ሥራዎች እነዚህ አካላት፣ ልምዳቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በማስተባበር በቁጭት መስራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከተማዋ በሀገር እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ ተመራጭና ተወዳዳሪነቷ እንዲጨምር በቀጣይ ለሚከናወነው የኮሪደር እና የሐይቅ ዳርቻ ልማት ስራ ርብርባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዕውቅና ከተሰጣቸው የሥራ ተቋራጮች መካከል የይርጋዓለም ኮንስትራክሽን ባለቤት ወይዘሮ ይርጋዓለም አስፋው የተሰጣቸው ዕውቅና በቀጣይ ሥራዎች ላይ የላቀ ሥራ ለመስራት እንደሚያተጋቸው ተናግረዋል፡፡
በግል አስተዋፅዖ እውቅና ከተሰጣቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ጋሻው ምትኬ (ዶ/ር) በበኩላቸው በተለይ በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ የአፈር አይነት መረጣ፣ የሚተከሉ ዕፅዋት ልየታ እና እንክብካቤ እንዲሁም ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ሙያዊ አበርክቶዎችን ያለክፍያ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ከተማዋ አምራና ደምቃ ሲመለከቷት የህሊና እርካታ እንደሚሰማቸው ጠቅሰው ለከተማቸው በዚህ መልኩ ሙያዊ ተሳትፎ ማድረጋቸውን እንደ እድለኝነት እንደሚቆጥሩት ነው የተናገሩት፡፡
አራተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ ከ3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር በላይ እንደሚሸፍን የተገለጸ ሲሆን በከተማዋ በሚገኘው የፍቅር ሀይቅ ዙሪያ የሚከናወነው የሀይቅ ዳርቻ ልማት የዲዛይን ስራ በመጠናቀቁ በቅርቡ ወደ ግንባታ እንደሚገባም ተጠቁሟል።