የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ ብቃቷን ያሳየችበት መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ ብቃቷን ያሳየችበት መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ ግዙፍ ስፖርታዊ ኹነቶችን የማስተናገድ አቅምና ብቃት እንዳላት በተግባር ያሳየችበት መድረክ መሆኑን የኢትዮጵያ ዝነኛ አትሌቶች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በ2027 የዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ውድድርን እንድታስተናግድ ዕድል በማግኘቷ ደስታ እንደተሰማቸውም ጠቅሰዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን ውድድር የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ትላንት በስኬት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት መሰረት ደፋር እንደገለጸችው፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዘዋወር ሲወዳደሩ ቆይተዋል።
እንዲህ ያሉ ውድድሮች በሀገራችን እንዲካሄዱ የነበረው ምኞት ዛሬ እውን በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።
የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር መካሄዱ ለአትሌቶቻችን ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል ነው ያለችው።
ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ በብቃት ማስተናገድ እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከረችበት መሆኑንም አትሌት መሠረት ገልጻለች።
በተመሳሳይ ታዋቂው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲኖሯት የሁልጊዜ ምኞቱ መሆኑን ያስታውሳል።
የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን ውድድር የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ መካሄዱ የረጅም ጊዜ ህልሙን ያሳካ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ ውድድሩን በስኬት ማስተናገዷ ለሀገር ትልቅ ኩራት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌቱ ገረመው ናቸው።
ከዚህም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሌሎች ውድድሮችን ለማስተናገድ በር የከፈተና ሀገራችን ትልቅ አመኔታ እንድታገኝ ያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይ የተሻሉ ዕድሎችን ለመጠቀም በስፖርት መሰረተ ልማትና በዝግጅት ረገድ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
አትሌት መሰረት ደፋር እና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ መንግሥት ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ያላትን ገናና ስም ለማስቀጠል ለዘርፉ ለሰጠው ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።
የተጀመሩ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በታሪካዊው የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር ላይ ከ70 በላይ ዓለም አቀፍ አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።