የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር የባህልና የወዳጅነት ትስስር የታየበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር የባህልና የወዳጅነት ትስስር የታየበት ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር የባህል ብልፅግና እና የወዳጅነት ትስስር ጠንክሮ የታየበት ነው ሲሉ የከተማዋ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።
የዓለም አትሌቲክስ የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ የአንድ ቀን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታዲየም በስኬት ትናንት ተካሂዷል።
ውድድሩ መጠናቀቁን ተከትሎም ለተወዳዳሪ አትሌቶች በአራዳ ፓርክ የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ የታሪክ፣ የእንግዳ ተቀባይነት እና የትስስር ከተማ መሆኗን በተግባር አረጋግጣለች።
ከተማዋ እንግዶቿን ተቀብላ ከማስተናገድ ባሻገር፣ እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው ማድረጓን ገልጸዋል።
ስፖርት የሚጠይቀውን ከፍተኛ ዲሲፕሊንና መስዋዕትነት እንዲሁም የሚፈጥረውን የተስፋ ስሜት ከተማዋ በሚገባ እንደምትረዳም አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ የተካሄደው ውድድር ከመወዳደሪያነት ባለፈ፣ የወዳጅነት ትስስር የተጠናከረበት፣ የህዝቡ ፍቅር እና የባህል ብልጽግና የታየበት፣ እንዲሁም የከተማዋ ልዩ መንፈስ የተንጸባረቀበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
አክለውም እንግዶቹ በከተማዋ የሚያሳልፉት እያንዳንዱ ቅጽበት የጋራ ታሪክ አካል እንደሚሆን ገልጸው፤ ቆይታቸው አስደሳች እና የማይረሳ ተሞክሮ እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የአዲስ አበባ ግራንድ ፕሪክስ ውድድር፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች ብቻ የሚሳተፉበት እና ዓለም አቀፍ አትሌቶች የሚሳተፉበት በሚል በሁለት ተከፍሎ ነበር የተካሄደው።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ብቻ የተሳተፉባቸው የሴቶችና የወንዶች የ10 ሺህ ሜትር፣ እንዲሁም የወንዶች የሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድሮች ትናንት ከእኩለ ቀን በፊት ተካሂደዋል።
በውድድሩም በሴቶች 10 ሺህ ሜትር፡ አትሌት ፋንታየ አዳነ፤ በወንዶች 10 ሺህ ሜትር፡ አትሌት ይስማው ድሉ እና በወንዶች ሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል አትሌት ገመቹ ጎዳና አንደኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል።
የዓለም አትሌቲክስ ውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች የተሳተፉበት ከመሆኑም በላይ፣ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ተጠቁሟል።