ቱሪዝም የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ቱሪዝም የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ እንደመሆኑ የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የገበታ ለትውልድ መርሐ-ግብር አካል የሆነው በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የሀሮ ደንዲ ሎጅ ዛሬ በይፋ መመረቃቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ይህ ስፍራ የተፈጥሮን ሥነ-ምኅዳር የጠበቀ የቱሪዝም መዳረሻ ከመሆኑ ባለፈ፤ ዘመናዊ ሥነ-ሕንጻ ከተፈጥሮ የልብ ትርታ ጋር የተዋሃደበት የኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ነው ብለዋል።
በዚህ ቦታ የቆመው ግንባታ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ይልቁንም የተፈጥሮ ቅርሳችንን በማክበር፣ የደንዲ ክሬተር ሐይቅን ነባራዊ ውበት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተርፍ አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባህላዊ እሴት ባከበረ እና ሰው ተኮር በሆነ መልኩ መሬቱን ለመንከባከብና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገነባ ስፍራ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
የሀሮ ደንዲ ሎጅ፤ የገባነውን ቃል ፈጽመን የመገኘታችን ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ሎጅው እና የአካባቢው አስደናቂ ሥነ-ምኅዳር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት፣ ለኢንቨስትመንት እና ለሁነት ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል በማለት ጠቅሰዋል።
ቱሪዝም የኢኮኖሚያችን አንዱ ምሰሶ እንደመሆኑ የሀገራዊ ዕድገታችንን የወደፊት አቅጣጫ እየቀረጸ ያለ ዘርፍ መሆኑን እያስመሰከረ ነው ሲሉም ተናግረዋል።