ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የሚቻለው በዜጎች ንቁ ተሳትፎ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የሚቻለው በዜጎች ንቁ ተሳትፎ ነው
ባህር ዳር፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት የሚቻለው በዜጎች ንቁ ተሳትፎ መሆኑን በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ህብረተሰብ በቀሩት የምዝገባ ቀናት ካርድ በማውጣት ድምጽ የመስጠት መብቱን እንዲጠቀምም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል (አዴሃን) ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዜጎች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡት ይወክለናል የሚሉትን ፓርቲ በመምረጥ በምርጫ መሳተፍ ሲችሉ ነው።
የምዝገባ ጊዜው ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ብቻ መቅረቱን ያስታወሱት ሰብሳቢው መራጮች በቀሪ ቀናት ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ማውጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
መራጩ ህብረተሰብ የውሳኔ ሰጪነት ዕድሉን ማባከን እንደሌለበት ያስገነዘቡት ሰብሳቢው እድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ዜጎች በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።
ዴሞክራሲ ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ ሰላማዊና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የሁሉንም ህብረተሰብ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎችም የምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን የስነ-ምግባር መመሪያና ሌሎች ህጎችን አክብረው በመንቀሳቀስ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ አሳስበዋል።
የሀገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን ከሚጎዱ ተግባራት መቆጠብ እንደሚገባ ጠቁመው በፓርቲዎች መካከል በፖሊሲ ልዩነት ቢኖርም በሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ላይ ልዩነት መፍጠር አይገባም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዚያ 14/2018 ዓ.ም መራዘሙን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን መራጮችም በቀሪ ጊዜ የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።