ቀጥታ፡

የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ተግባራዊ የተደረጉ የተለያዩ ኢንቬቲቮች ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥተዋል

ጅማ ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በለውጡ ዓመታት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ተግባራዊ የተደረጉ የተለያዩ ኢንቬቲቮች ተጨባጭ ውጤቶች ማምጣታቸውን በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ  ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ነመራ ቡሊ ገለጹ።

ብልጽግና ፓርቲ በጅማ የምርጫ ምልክትና ማኒፌስቶውን ለህዝብ የማስተዋወቅ መርሃግብር አካሄዷል።


 

በሁነቱ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ነመራ ቡሊ፣ ባለፉት ዓመታት ዜጎችን ከድህነት በማውጣት ወደ ተሻለ ህይወት ለማሻገር የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በለውጡ ዓመታት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ተግባራዊ የተደረጉ የተለያዩ ኢንቬቲቮች ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥተዋል ብለዋል።

በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ ዘርፎች በመትጋት ዘላቂ ሰላምና ልማትን በማረጋገጥ እንዲሁም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማፅናት ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶችን ዘርዝረዋል። 


 

በመደመር እሳቤ ዘመናዊና አሳታፊ የፖለቲካ ስርአት መገንባት ተችሏልም ብለዋል።

የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር፣ የጅማ ዞንና ከተማዋ ከለውጡ በፊት ምን ይመስል እንደነበር በማስታወስ ከለውጡ በኋላ የተሰራውን ማየት ለስኬቱ ጥሩ ማሳያ ስለመሆኑ አንስተዋል። 


 

በቀጣይ ይህንን ስኬት ለማስቀጠል ከህዝቡ ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

የጅማ ከተማ ከንቲባ ጠሃ ቀመር፣ የጅማ ከተማ ልማት ለከተሞች ለውጥና ማንሰራራት ሁነኛ ማሳያ ስለመሆኑ ገልፀዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የፓርቲው አመራሮችና አባላት፣ ደጋፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም