የሚበጀንን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ወስደን ተዘጋጅተናል-የዋጂፎ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሚበጀንን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ወስደን ተዘጋጅተናል-የዋጂፎ ከተማ ነዋሪዎች
ዋጂፎ፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- በጠቅላላ ምርጫው በመሳተፍ የሚበጃቸውን ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ወስደው መዘጋጀታቸውን በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ የዋጂፎ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
እስከፊታችን ሚያዝያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የተራዘመው የመራጭነት ምዝገባ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል።
የመመዝገቢያ ቀኑ ሳይጠናቀቅ ቀድመን ካርድ ወስደናል የሚሉት በምዕራብ አባያ ወረዳ የዋጂፎ ከተማ ነዋሪዎች በምርጫው ላይ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ አንዴቦ አዳዬ እንደሚሉት ባለፉት ስድስት የምርጫ ጊዜያት በመሳተፍ ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ ሲመርጡ ቆይተዋል።
ይህንን ልምድ በመጠቀም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
የመራጮች ምዝገባ ጊዜ መራዘሙ ዕድሜያቸው ለመራጭነት የደረሰ ሁሉ ካርድ እንዲወስድ ተጨማሪ ዕድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ደንሳ ኡርቃቶ ናቸው።
ካርድ ቀድሜ በመውሰድ ለምርጫው ተዘጋጅችያለሁ ያሉት አቶ ዳንሳ፤ በምርጫውም ዕለት ድምጼን ለመስጠት እየተጠባበኩ ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ወግደረስ አዘዘ በበኩላቸው፤ በምርጫ መሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ ቀድመው ወስደዋል።
መምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እንደሆነ ተገንዝበው ካርድ መውሰዳቸውንና የሚበጃቸውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ሴቶች በተሰጣቸው የመምረጥና የመመረጥ ዕድል ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።