ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከቀኑ 10 ሰዓት ሲዳማ ቡና ድሬዳዋ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። 

ሲዳማ ቡና በ51 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል። ድሬዳዋ በ32 ነጥብ 15ኛ ይዟል።

በ27ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1 ለ 0 የረታው ሲዳማ ማሸነፍ መሪነቱን እንዲያጠናክር ያስችለዋል።

በመቻል በ27ኛው ሳምንት 2 ለ 1 የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ መቻል ከሃዋሳ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው።

መቻል በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሃዋሳ ከተማ በ42 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው መቻል ማሸነፍ በድል ጉዞው እንዲቀጥል ከማስቻሉ ባሻገር ወደ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል። 

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ማሸነፍ ግድ ይለዋል። 

በሌላኛው መርሐ ግብር ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከሀድያ ሆሳዕና በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ነገሌ አርሲ በ43 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟልል። ሀድያ ሆሳዕና በ33 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ነገሌ አርሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል። 

በ27ኛ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሁለት አቻ የወጣው ሀድያ ሆሳዕና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኢትዮጵያ ቡና በ37 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። 

አርባምንጭ ከተማ በ23 ነጥብ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሁለቱ ቡድኖች በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፉም። 

ቡድኖቹ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም