ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከደቡብ ሱዳን ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2018 (ኢዜአ)፦  በ10ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ቅድመ ማጣሪያ ኢትዮጵያ የመልስ ጨዋታዋን ዛሬ ከደቡብ ሱዳን ጋር ታደርጋለች።

ጨዋታው ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ  በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ሁለቱ ሀገራት ሚያዚያ 4 ቀን 2018 ዓ.ም በጁባ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በቤተልሔም ግዛቸው እና ምኀረት አየለ ጎሎች 2 ለ 0 አሸንፋለች።

በራውዳ አሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጁባ ከተመለሰ በኋላ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅቱን ሲያደርግ መቆየቱንና ትናንት ደግሞ የመጨረሻ ልምምዱን ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በሞሰስ ዛካሪያ ንጎር የሚሰለጥነው የደቡብ ሱዳን ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን  ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን የመጨረሻ ልምምዱንም ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አከናውኗል።

ኢትዮጵያ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈች በሁለተኛው ዙር ከብሩንዲ  ጋር ትጫወታለች።   

ትናንት በተደረገ የመልስ ጨዋታ ብሩንዲ ማላዊን 2 ለ 1 በማሸነፍ በአጠቃላይ ድምር ውጤት ተጋጣሚዋን 4 ለ 2 በመርታት ወደ ሁለተኛው ዙር አልፋለች። 

10ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት ሴቶች የዓለም ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 7 እስከ ጥቅምት 28 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ። በዓለም ዋንጫው አፍሪካ ሞሮኮን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ትወከላለች። 

በማጣሪያ የሚያልፉ አራት የአፍሪካ ሀገራት በሶስት ዙሮች በሚደረጉ ጨዋታዎች ይለያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም