በሸገር ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው
ሸገር፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለኢንቨስትመንት ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን የከተማዋ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኃላፊ መኮንን አምባው ገለጹ።
ኃላፊው ለኢዜአ እንዳሉት፤ መሶብ በሁሉም ዘርፎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ለኢንቨስትመንት ሥራዎች መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ይህንን የአንድ ማዕከል አገልግሎት በይበልጥ ለማጠናከር የከተማው አስተዳደር በከተማ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክፍለ ከተሞችም ጭምር ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ ተገልጋዮች የሚፈልጉትን አገልግሎት በአንድ ቦታ በፍትሐዊነት እንዲያገኙ እያደረገ በመሆኑ የከተማዋን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይበልጥ ቀልጣፋ እያደረገው ነው ብለዋል።
ይህንን ሥራ ይበልጥ ለማጠናከር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን ወደ ተንቀሳቃሽነት በመለወጥ ዘርፉን በቅርበት ለማገልገል ሰፊ ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።
በከተማዋ 32 የተለያዩ ሴክተሮችን በአንድ ማዕከል በማገናኘት ማኅበረሰቡ ቀልጣፋና ግልጽነት ያለው አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በማዕከሉ 159 የሥራ ዓይነቶች አገልግሎት እየተሰጠባቸው መሆኑን ገልጸው፤ ከመደበኛ የሥራ ቀናት በተጨማሪ በምሳ ሠዓትና በእሁድ ቀናትም አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሸገር ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታን የፈጠረና የአገልግሎት አሰጣጥ ዕርካታን ያረጋገጠ መሆኑን የከተማዋ ተገልጋዮች ገልጸዋል።