ቀጥታ፡

በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው በመመለስ የልማት ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡-በኢ-መደበኛ ፍልሰት ወደ መካከለኛው ምስራቅና ሌሎች አካባቢዎች ተጉዘው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው በመመለስ፣ በልማት ስራዎች ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

መንግሥት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተል በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ተጨባጭ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ተሰማርተው መስራት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በመፈረም ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያውያን በውጭ ሀገራት መብታቸው ተከብሮ የላባቸውን ዋጋ እንዲያገኙ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ሕጋዊ አሰራርን ተከትለው ከመሄድ ይልቅ በኢ-መደበኛ ፍልሰት ከሀገር የሚወጡ ዜጎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ይህም ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለሥነ ልቦናዊ ቀውስ የሚዳርግ የተሳሳተ መንገድ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።  

በመካከለኛው ምስራቅና ሌሎች አካባቢዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ከመመለስ ባለፈ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ተመላሾችን በሀገራቸው ሠርተው እንዲለወጡና  የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሥርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።

በውጭ ሀገራት ሠርተው የመለወጥ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ራሳቸውን ከተለያዩ ተጋላጭነቶች ለመጠበቅ፣ መንግሥት የዘረጋውን ሕጋዊና መደበኛ የጉዞ ሥርዓት ብቻ ሊከተሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም