ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎች ቀጣይነት ያለውን ጠንካራ ድጋፍ አረጋገጠ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎች ቀጣይነት ያለውን ጠንካራ ድጋፍ አረጋገጠ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 11/2018 (ኢዜአ)፡- ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ ያከናወነችው ሪፎርም ያመጣውን መሻሻል በማድነቅ ለሀገሪቱ የሪፎርም አጀንዳ ያለውን ጠንካራ ድጋፍ ዳግም አረጋግጧል።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂየቫ ጋር ተወያይቷል።
ውይይቱ የተካሄደው፤ ከ2026 የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የፀደይ ስብሰባ ጎን ለጎን መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።
በምክክሩ ወቅትም፤ በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አማካኝነት እየተመዘገቡ ያሉ ቀጣይነት ያላቸው ውጤቶችን ልዑኩ አብራርቷል።
ለአብነትም በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገትና የዋጋ ግሽበት መቀነስን ጨምሮ ሌሎች አዎንታዊ አዝማሚያዎች መታየታቸውን ጠቁሟል።
ሪፎርሙ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተውን ወቅታዊ ሁኔታ ጨምሮ የሚከሰቱ ውጫዊ ተፅዕኖዎችን ተቋቁሞ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉም ተብራርቷል።
ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ከአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል፣ ከነዳጅ ብሎም ማዳበሪያ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ጫናዎች መኖራቸውም እንዲሁ።
እነዚህን ወቅታዊ ችግሮች ለመሻገርም የተጠናከረ ዓለም አቀፍ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝቧል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ያከናወነችው ሪፎርም ያመጣውን መሻሻል በማድነቅ፤ተቋማቸው ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ሪፎርሙን ለማስቀጠል እና የፋይናንስ ፍላጎቶችን ለማሟላት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።