ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል ፦ የዋንጫው ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ታላቅ ፍልሚያ - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል ፦ የዋንጫው ዕጣ ፈንታ የሚወሰንበት ታላቅ ፍልሚያ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 11/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 33ኛ ሳምንት ማንችስተር ሲቲ ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያንን ቀልብ ስቧል።
ጨዋታው ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ በኢትሃድ ስታዲየም ይካሄዳል።
ማንችስተር ሲቲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ64 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አርሰናል በ70 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ሁለቱ ክለቦች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ58ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም በነበራቸው 57 የሊግ ግንኙነት አርሰናል 25ቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 19 ጊዜ ድል ሲቀናው በቀሪ 13 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በ57ቱ ጨዋታዎች አርሰናል 82 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ ማንችስተር ሲቲ 75 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ቡድኖቹ ባለፉት 10 የሊግ ግንኙነታቸው ሲቲ አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል በሁለቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በአምስተኛ ሳምንት በኤምሬትስ ስታዲየም ባደረጉት የሊግ ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በ32ኛ ሳምንት አርሰናል በቦርንማዝውዝ 2 ለ 1 መሸነፉና ማንችስተር ሲቲ ቼልሲን 3 ለ 0 ማሸነፉ የዋንጫው ፉክክር ላይ ዳግም ነፍስ ዘርቷል።
ባለሜዳው ማንችስተር ሲቲ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ እንዲያደርግ ያስችለዋል።
አርሰናል ድል ከቀናው ዋንጫ የማንሳት እድሉ የበለጠ ሰፊ ይሆናል።
ይህ የማንችስተር ሲቲ እና የአርሰናል ግጥሚያ በብዙዎች ዘንድ 'የዘንድሮውን የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ መዳረሻን የሚበይን' ታላቅ ፍልሚያ ተብሎ ተፈርጇል።
የ47 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች ጨዋታዎች ኤቨርተን ከሊቨርፑል ከቀኑ 10 ሰዓት በሂል ዲኪንሰን ስታዲየም የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል።
አስቶንቪላ ከሰንደርላንድ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ከበርንሌይ በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።