ቀጥታ፡

የአብሮነት እሴቶችን የበለጠ ለማጎልበት በጋራ መስራት ያስፈልጋል - መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ) ፦ የአብሮነት እሴቶችን የበለጠ ለማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

‘ከፍልስፍና ወደ ዕለታዊ ተግባር‘ በሚል መሪ ሀሳብ በእውነቱ ሀይሉ (ዶ/ር) የተጻፈው "The Ubuntu Rule of Five" (የኡቡንቱ አምስቱ ደንቦች) የተሰኘ መጽሀፍ የተቋማት ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ከተለያዩ ዘርፍ የተወጣጡ ባለሙያዎች በተገኙበት የመጽሐፍ ምረቃና ውይይት ተካሂዷል።


 

መጽሀፉ የአፍሪካውያን የአብሮነትና የሰብዓዊነት እሴቶች ላይ ባተኮረው የኡቡንቱ ፍልስፍና መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው።

ቀደም ሲል በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ለህትመት መብቃቱም ተገልጿል።

አሁን ደግሞ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ አንባቢያን ተደራሽ ለማድረግ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለንባብ መብቃቱ ተጠቅሷል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንደገለጹት፤ የአብሮነት እሴቶችን የበለጠ ለማጎልበት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ።

በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰቱ ግጭቶችንና ቁርሾዎችን ለመፍታት መመካከርና መደማመጥ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክር የትውልድ ስብራትን ለመጠገን አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገራዊ ምክክር ቀርበዋል ብለዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቃው መጽሀፍ የአፍሪካውያን እሴት ከኢትዮጵያውያን እሴቶች ጋር በማጣጣም የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሀገራዊ ምክክሩ ሀገር በቀል እሴቶች ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው በመሆኑ በመጽሀፉ የተካተቱ የሀገሪቷ እሴቶች ለምክክሩ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአፍሪካ የኡቡንቱ እሴት ለሀገርና ለዓለም ጠቃሚ የሆነ ሀብት ነው ብለዋል።

መጽሀፉ የአብሮነት እሴትን በስፋት ለመተግበር የሚያሰችል መሆኑንም ነው የገለጹት።

አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ፤ አብሮነት ለሁላችንም የሚበጅ ነው፤ በኪነ ጥበብ ስራዎቻችን አብሮነትን የሚሰብኩ አስታራቂ ታሪኮችን በስፋት ለህበረተሰቡ ማቅረብ አለብን ሲል ተናግሯል።

መጽሀፉ ግለሰባዊና ጠባብ አመለካከትን በማስቀረት አብሮነትን ለማጎልበት የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚያመላክት ነው ብሏል።

በጅማ ዩኒቨርሰቲ መምህርና "The Ubuntu Rule of Five" የተሰኘው መጽሀፍ ጸሀፊ በእውነቱ ሀይሉ(ዶ/ር)፤ የኡቡንቱ አስተሳሰብ ከቃል ያለፈ ለአፍሪካውያን የተለየ ትርጉም ያለው ለአብሮነትና ለምክክር መሰረት ነው ብለዋል።

አስተሳሰቡ ለኢትዮጵያውያን የአንድነት ገመድ ስሪታችን የተቋጨበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም