ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የልማት ስኬት መዲናዋን የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ማዕከል እያደረጋት ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የልማት ስኬት መዲናዋን የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ማዕከል እያደረጋት ነው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለ30ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምል የፖሊስ ሠራዊት አባላት አስመርቋል።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት፤ የአዲስ አበባ የልማት ስኬት መዲናዋን የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ማዕከል እያደረጋት ነው ብለዋል።

ለዚህም በመዲናዋ ነዋሪዎችና የፀጥታ አካላት ቅንጅት አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ የኮንፈረንስ ቱሪዝምና የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ወሳኝ ሚና እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላትም የሰላም ግንባታ ተልዕኮን በብቃት በመወጣት ህዝባቸውን በከፍተኛ ኃላፊነትና ታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው፤ ሙያዊ ክህሎት የተላበሰ እና ሙያዊ ግዳጅን በላቀ ብቃት የሚፈጽም የፖሊስ ሠራዊት ተገንብቷል ብለዋል።


 

በተቋሙ የተወሰደው የሪፎርም እርምጃም የመዲናዋን ሰላም በማፅናት ግዙፍ የልማትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚያፋጥን ወሳኝ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ተመራቂ የሠራዊት አባላቱም የመጪውን ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊነት በማስጠበቅ ግዳጁን በብቃት መወጣት የሚያስችል የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ተመራቂ የፖሊስ አባላት በበኩላቸው፤ በስልጠና ቆይታቸው ግዳጅን በብቃት መወጣት የሚያስችል የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ዕውቀትና ክህሎት መቅሰማቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን አደራ በብቃት በመወጣት ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ኮንስታብል ቢኒያም ተሾመ ሥራዬን በታማኝነት በመከወን የሕዝብ አደራ በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል።

ኮንስታብል እንግዳየሁ አስረስ በበኩሉ፤ የአዲስ አበባ ጠቅላይ መምሪያ በሚሰጠን አቅጣጫ መሰረት ማንኛውንም ግዳጅ ለመፈጸም ተዘጋጅቻለሁ ሲል ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም