ቀጥታ፡

በአስተዳደሩ የሕጻናት መቀንጨርን ለማስቀረት የሥርዓተ ምግብ ሞዴል መንደሮችን በመመስረት እየተሰራ ነው

ሰቆጣ፤ ሚያዚያ10/2018 (ኢዜአ)፡-በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሕጻናት መቀንጨርን ለማስቀረት የሥርዓተ ምግብ ሞዴል መንደሮች መመስረታቸውን የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የስርዓተ ምግብ ባለሙያ ወይዘሮ ወርቅ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የመቀንጨር ችግር ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው።

መምሪያው ከሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህብረተሰቡን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የተመጣጠነ ምግብ የመመገብ ባህሉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

እናቶች በጓሮ አትክልት፣ በዶሮና ፍየል እርባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲመግቡ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ህጻናት ልጆቻቸውን በንጥረ ነገር የበለፀጉ አትክልት፣ ሥጋና ጥራጥሬ ምግቦችን በመመገብ ጤንነታቸው እንዲጠበቅና  የተስተካከለ እድገት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በእዚህም በአስተዳደሩ በሥርዓተ ምግብ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ባሳዩ 69 ቀበሌዎች 82 ሞዴል መንደሮች መመስረቱን ባለሙያዋ ተናግረዋል።

በእያንዳንዱ መንደር 60 የሚያጠቡ ነፍሰ ጡር እናቶችን በማሳተፍ ስርዓተ ምግብን በሚያሳድጉ የጓሮ አትክልትና የእንስሳት እርባታ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል።

የመንደር ምስረታውን ወደ ሌሎች ቀበሌዎችና ወረዳዎች በማስፋት በሕፃናት ላይ የሚያጋጥመውን የመቀንጨር ችግር ሙሉ በሙሉ ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በደሃና ወረዳ ዳብጦ ሞዴል መንደር ነዋሪ ወይዘሮ ገነት ደባሽ እንዳሉት በስርዓተ ምግብ ዙሪያ በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት የጓሮ አትክልትና የዶሮ እርባታ ሥራ እያከናወኑ ነው።

በእዚህም የጓሮ አትክልትና እንቁላልን ከተለያዩ ምግቦች ጋር በማሰባጠር ልጆቼን ለመመገብ ችያለሁ ብለዋል።

በተደረገልን የጥቅል ጎመንና የቆስጣ ዘር ድጋፍ በጓሯችን የጓሮ አትክልት አልምተን ለመጠቀም ችለናል ያሉት ደግሞ በአበርገሌ ወረዳ የሳቃ መንደር ነዋሪ ወይዘሮ እሸሽ እሉ ናቸው።

የጓሮ አትክልት ልማት ሥራቸው ልጆቻችውን የተመጣጠነ ምግም ለመመገብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ የሕጻናት መቀንጨር ችግር ከሚስተዋልባቸው የተከዜ ተፋሰስ አካባቢዎች ውስጥ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዱ ነው።

በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት መሰረት መንግስት በሀገር በቀል መፍትሄ መሰረት ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን የመቀንጨር ችግር በ2022 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ግብ አስቀምጦ እየሰራ ነው።

በዚህም በተከዜና ሌሎች አካባቢዎች ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡርና ወላድ ህጻናት ላይ የሥርአተ ምግብን ለማሻሻል በሚከናወኑ ተግባራት ውጤት እየታየ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን በማሻሻል የሕጻናትን ጤና፣ እድገትና ልማት ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተም ይገኛል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም