አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ አንጋፋ ዲፕሎማት ነበሩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ አንጋፋ ዲፕሎማት ነበሩ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ አንጋፋ ዲፕሎማት እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለፁ።
አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የአንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ በእንጦጦ ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት አንድነት ገዳም መካነ መቃብር ተፈፅሟል።
በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ የሱፍ፣ የሀገራት አምባሳደሮችና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ አምባሳደር ቆንጅት በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሀገራቸውን ያገለገሉ ብርቱ ዲፕሎማት ነበሩ።
አምባሳደሯም በተለያዩ ሀገራት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ደግሞ በቋሚ መልዕክተኛነት ሀገራቸውን በታላቅ ኃላፊነት ማገልገላቸውን ገልጸዋል።
አምባሳደር ቆንጂት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ዘመናቸውም ለበርካታ ዲፕሎማቶች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ጠንካራና ታታሪ ዲፕሎማት እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የከፍታ ጉዞም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ አንጋፋና የሀገር ባለውለታ ዲፕሎማት እንደነበሩ አንስተዋል።
የዲፕሎማሲ ስራ በሰዓት ሳይገደብ ሙሉ ጊዜና ትኩረት በመስጠት የሚከወን እንደሆነ ያስተማሩም ጭምር መሆናቸው ጠቅሰዋል።
በጡረታ ከተገለሉ በኋላም እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ከአፍሪካ ህብረት ስራዎች በዲፕሎማሲ ዘርፉ ሲያገለግሉ መቆየታቸው ተናግረዋል።
አምባሳደር ቆንጂት በህይወት በነበሩበት ወቅት በርካታ ጠንካራ ዲፕሎማቶች ያፈሩ እንደነበሩ ገልፀው፤ በቀጣይም ወጣት ዲፕሎማቶች ከሳቸው ልምድና የህይወት ተሞክሮ ተምረው በመማር ሀገራቸው ለማገልገል ትልቅ መነሳሳት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1950ዎቹ በለጋ እድሜያቸውተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ማገልገላቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በ1932 ዓ.ም በሐረር ከተማ የተወለዱት አምባሳደር ቆንጂት ከዮዲት እምሩ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደር በመሆን ሀገራቸውን ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል።
አምባሳደሯም በኦቶዋ፣ ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬይና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት፤ በአፍሪካ ሕብረትና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በቋሚ መልዕክተኛነት ሰርተዋል።
ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011 ዓ.ም ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ልዩ አማካሪ ነበሩ።