በክልሉ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ እንዲሆኑ በቅንጅት እየተሰራ ነው
ቦንጋ፤ ሚያዚያ 9/2018 (ኢዜአ)-ተማሪዎች በ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ሀላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) በክልሉ በመደበኛ፣ በማታና በርቀት 15 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በሃገር አቀፍ ፈተናው ውጤታማ እንዲሆኑ በፈረቃ እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱና ማታም ጥምር ቤተመጻህፍት እንዲጠቀሙ መደረጉን አንስተዋል።
በትምህርታቸው የተሻሉ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች በቋሚነት ትምህርት ቤት ውስጥ አድረው እንዲያጠኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሚፈለገው መጠን ተማሪዎቻቸውን ወደዩኒቨርሲቲ ላላስገቡ ትምህርት ቤቶች ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ልዩ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑ በትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት መሰረተ ልማት ዝርጋታና ሌሎች ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ፈተናው ውጤታማ ለመሆን ዝግጅታቸውን ማጠናከራቸውን የገለጹት ደግሞ የቦንጋ የመሀል ከተማ እና የቢሻው ወልደዮሐንስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ናቸው።
በሀገር አቀፍ ፈተናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅታቸውን እያጠናከሩ እንደሆነ ከገለጹ ተማሪዎች መካከል የመሀል ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተማሪ እዮብ እምሩ እና ተማሪ ፍቅራለም አቱሞ ይገኙበታል።
ትምህርት ቤቱ ከመደበኛ ትምህርት ክፍለ ግዜ በተጨማሪ የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ትምህርት በትጋት እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በግልና ከጓደኞቻቸውጋር በመሆን ጠንክረው እያጠኑ መሆናቸውንና የፈተና ጥያቄዎችን በመስራት ለፈተናው እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የቢሻው ወልደዮሐንስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ተግባሩ ተስፋዬ እና ተክልዬ ተሾመ እንዳሉት፣ በውጤታቸው ተመርጠው በትምህርት ቤቱ ውስጥ አድረው እንዲያጠኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እድል ፈጥሯል ።
በትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርትና በግላቸው የሚያደርጉት ዝግጅት በሀገር አቀፍ ፈተና ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል።
ከማጠናከሪያ ትምህርት ባለፈ ፈተናው በበይነ መረብ ለመውሰድም የቴክኖሎጂ ድጋፍና የስነ ልቦና ዝግጅት እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ የባዮሎጂ ትምህርት መምህር ቆጭቶ ገብረማሪያም ተፈታኝ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በማጠናከሪያ ትምህርት ከሚደረገው ድጋፍ ባለፈ በስነልቦናም የማብቃት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቢሻው ወልደዮሐንስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ጌታቸው መኮንን በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ በአዳሪና በመደበኛ 336 ተፈታኝ ተማሪዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ተማሪዎቹን ለሀገር አቀፍ ፈተና ለማብቃት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከመደበኛው ትምህርት በተጨማሪ በተቃራኒ ፈረቃና በቅዳሜና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥና በሞዴል ፈተናዎች የማለማመድ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መምህሩ አክለውም እንደገለጹት ተማሪዎችን በቴክኖሎጂ ብቁ ማድረግ የሚያስችል ድጋፍና በስነ ልቦናም የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡