የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ስኬት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን የሚያሳልጥ ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ስኬት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን የሚያሳልጥ ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ስኬት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን የሚያሳልጥ ወሳኝ ዕድል መፍጠሩን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ።
''ኢትዮጵያ ትገነባለች፤ ፈጠራ፣ ፍጥነትና ጥራት ለመሰረተ ልማት እመርታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማትና ኮንስትራክሽን ሳምንት እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሁለተኛ ቀኑን ይዞ በቀጠለው መድረክ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት ትስስርና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
እነዚህ ስኬቶችም የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ውጤታማነትን በማሻሻል አዲስ የኢኮኖሚ ዕድገት የለውጥ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ትስስርን የሚያሳልጡ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን የኢትዮጵያ መንገዶች ግንባታ እስከ ኤክስፕረስ መንገድ ያለው ዕምቅ አቅምና ቀጣይ ተስፋ የሚል የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በጽሑፋቸውም፤ የኢትዮጵያ መንገዶች እ.አ.አ. በ1997 ከነበረበት 26 ሺህ 550 ኪሎ ሜትር በ2025 ከ180 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ጥራት ያለው የመንገድ መሰረተ ልማት መገንባቱን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የመንገድ ልማት ሽፋንም ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የመንግስት፣ የልማት አጋሮችንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን የበጀት ትብብር በማጠናከር እ.አ.አ በ2030 የመንገድ ሽፋንን 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው፤ የኢትዮጵያን የባቡር ልማትና ቀጣናዊ ትስስር የሚዳስስ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የባቡር መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድትን በማፋጠን ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርን ለማጠናከር የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በቀጣይም የባቡር መሰረተ ልማት ሥራዎችን የሚያፋጥን ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ በገጠር ትስስር ዙሪያ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት መሀመድ አሚን በበኩላቸው፤ የከተማና ገጠር ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ትስስርን የሚያጠናክር የመንገድ መሰረተ ልማት እየተገነባ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማት ትስስር የአርሶና አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያሳለጠ መሆኑን አስገንዝበዋል።