የሽብርና ፅንፈኛ ኃይሎችን ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 138 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የሽብርና ፅንፈኛ ኃይሎችን ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 138 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የሽብርና ፅንፈኛ ኃይሎችን ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 138 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ እንዳመለከተው ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈፀም ታጥቀው በጫካ ከሚንቀሳቀሱ የሽብርና ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሀገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማወክ እንዲሁም መጪውን ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ ስምሪት ወስደው ሲንቀሳቀሱ ነው።
በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የጥፋት ስምሪት ወስደው ሲንቀሳቀሱ በነበሩት ተጠርጣሪዎች ላይ በጥብቅ ዲሲፕሊን የመረጃ ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቶ ከፌደራልና ክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከሚያዚያ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች እንዲሁም በተመረጡ አካባቢዎች ሽብር እና አመፅ በመቀስቀስ፤ ለታጠቁ ቡድኖች ሴሎችን በማደራጀት፤ መረጃዎችን በመስጠት፤ ጥቃትና እገታ ላይ በመሰማራት ተልዕኮ ወስደው ሲፈፅሙ የነበሩ መሆናቸው በመግለጫው ተብራርቷል።
ለሽብርና ፅንፈኛ ቡድኖች ገንዘብ፣ ስንቅ፣ ወታደራዊ አልባሳት፣ መገናኛ ሬዲዮዎች፣ የስልክ ቀፎዎችንና ሲም ካርዶችን፣ ጦር መሣሪያና ተተኳሾችን በአጠቃላይ ሎጀስቲክስ ሲያሰባስቡና ሲያቀርቡ እንደነበር እንዲሁም በተመረጡ ከተሞችና ቀበሌዎች የምርጫ እንቅስቃሴዎችን ለማደናቀፍ፣ ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶችን ጭምር ለመቀስቀስ ስምሪት የወሰዱ ስለመሆናቸውም መረጋገጡም ተመላክቷል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የተወሰኑት አልሸባብና አይ ኤስ ከተባሉት ዓለም-አቀፍ አሸባሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በሶማሊያ የሽብር ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውም በመረጃ ስምሪት ተረጋግጧል፡፡
በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ለቡድኖቹ ሴሎችን በመመልመል ለሽብር ተግባር ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ የነበሩ መሆናቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በኦፕሬሽኑ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ በመሰማራት ለሽብርና ለፅንፈኛ ቡድኖች ትጥቅና ተተኳሽ በማቅረብ የሀገራችን የፀጥታ ሁኔታ ለማባባስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።
እንዲሁም በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና የኮትሮባንድ ንግድ ላይ በመሰማራት የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር በመሰረታዊ የፍጆታ ምርት አቅርቦት ላይ እጥረት እንዲፈጠር ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውም ተረጋግጧል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ለሽብር እና ለፅንፈኛ ቡድኖች ሊተላለፉ በዝግጅት ላይ የነበሩ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችና ቦንቦች፣ ተተኳሾች፣ የተለያዩ የውጭ ሀገር የገንዘብ ኖቶች እንዲሁም የኮንትሮባንድ እቃዎች አብረው እንደተያዙ በመግለጫው ተጠቅሷል።
በተጠቀሱት ዝርዝር የሽብር እንቅስቃሴዎች ጨምሮ በተለያዩ የጥፋት ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው የነበሩ በድምሩ 138 ተጠርጣሪዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሕግ ቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉ ተመላክቷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሽብር እና የጥፋት ቡድኖችን ድብቅ ፍላጎት ለማክሸፍና የግንኙነት መረባቸውን ለመበጣጠስ ተጨማሪ ክትትሎችን እና ጥናቶችን እያደረገ እንደሆነ፤ በተለይም መጪው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊውን ቅድመ-ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ኅብረተሰቡም ይህን በመረዳት የተለመደውን ቀና ትብብርና ተሳትፎ በማድረግ መሰል የጥፋት ድርጊቶችን በመጠቆም ከአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እና ከመላው የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች ጎን እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል።