በምስራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 95 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 95 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተዋል
ነቀምቴ ፤ሚያዚያ 10/2018 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 95 ሺህ ወጣቶች ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች መሰማራታቸውን የዞኑ የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ባጩ ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጽሕፈት ቤቱ የሥራ አጥነትን ችግር በማቃለል የአምራች ኃይሉን የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱም ከ100 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት የታቀደ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ሒደት 95 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል ግብርና እና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ ሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን በአብነት ጠቅሰዋል።
ወጣቶቹ በተሰማሩባቸው መስኮች ውጤታማ መሆን እንዲችሉም መንግሥት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር እንዳመቻቸላቸው ተናግረዋል።
ይህም የዞኑን ወጣቶች የሥራ ባሕል በመቀየር የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በዞኑ የሲቡ ስሬ ወረዳ የንግድ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብሳ ዲለንሳ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ከጠባቂነት ተላቀው ባላቸው ዕውቀት እና ጉልበት ሠርተው እንዲለወጡ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ በበጀት ዓመቱ ከ9 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ታቅዶ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ወጣቶቹን በ340 ኢንተርፕራይዞች በማደራጀት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት ማደለብና እርባታ፣ እንዲሁም በሌሎች መስኮች በመሰማራት የተሻለ ውጤት በማምጣት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የወረዳው አስተዳደርም ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በማቅረብ ኢንተርፕራይዞቹ እንዲጠናከሩ ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል።
ከሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎች መካከል በብረታ ብረትና እንጨት ሥራ የተሰማራው ጪምዴሳ በዳሳ እንደሚለው፤ በዚህ ዓመት መንግሥት ባመቻቸላቸው ዕድል የ200 ሺህ ብር ብድር በመውሰድ ሥራ ጀምረዋል።
በተመቻቸላቸው ዕድል ጠንክረው በመሥራትም ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ይናገራል።
በአሁኑ ወቅትም ካፒታላቸውን ወደ 1 ሚሊዮን ብር በማሳደግ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክቷል።
በወረዳው የሚገኙት የጫልቱ፣ ዓለምነሽ እና ጓደኞቻቸው ማህበር አባል ወጣት ምቲኬ አበራ፤ በተያዘው ዓመት በእንጀራ ንግድ ላይ ሥራ የጀመረው ማኅበራቸው ጥሩ ገቢ ማግኘት መጀመሩን ተናግራለች።