ዛሬ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድርን በአዲስ አበባ በድምቀት አስተናግዳለች - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ዛሬ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድርን በአዲስ አበባ በድምቀት አስተናግዳለች - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ ዛሬ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድርን በአዲስ አበባ በድምቀት ማስተናገዷን ከንቲባ አዳነች አበቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ይህ ስኬት በከተማችን የገነባናቸው ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች ውጤት ከመሆኑም ባለፈ፣ አገራችን በአትሌቲክስ ዘርፍ ያላትን ታላቅ ዝና ዳግም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በሚያዝያ ወር ብቻ የምናስተናግዳቸው ሦስት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች፣ ከተማችን ማንኛውንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ውድድር የማስተናገድ ብቃትና ደረጃ ላይ መድረሷን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
እነዚህ ውድድሮች ተተኪ አትሌቶችን ከማነቃቃታቸውም በላይ ለስፖርታዊ ቱሪዝም ዕድገት የጎላ ፋይዳ አላቸው።
ይህ ታሪካዊ ውድድር በአዲስ አበባ መካሄዱ ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹና ሳቢ ከማድረግ ባለፈ፣ ለዓለም አቀፍ ኩነቶች ማራኪ የስበት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን በተግባር ያሳየ እውነት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የተለመደውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት ላሳዩት ስፖርት ወዳድ ነዋሪዎችም በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።
ለእንግዶቻችን በቆንጆዋ አዲስ አበባ የማይረሳና ያማረ ቆይታ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት።