ቀጥታ፡

ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል

ወልቂጤ፤ ሚያዚያ10/2018 (ኢዜአ):-ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባን  እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ማራዘሙ ይታወቃል።

ይህም በተለያየ ምክንያት የመራጭነት ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ ዕድል ያመቻቸ ነው። 

የጉራጌ ዞን ነዋሪዎችም ለመራጭነት የሚያበቃቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ለሃገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ነው የተናገሩት።

በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ ጋህራድ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዱ ሽኩር ይወክለኛል ለሃገር ሰላምና ልማት ይሰራል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለመራጭነት እድሜው የደረሰ  ዜጋ የመራጭነት ካርድ ሊያወጣ እንደሚገባ የመከሩት አርሶ አደር አብዱ፣ በድምጻቸው ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫውን እለት  እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወልቂጤ ከተማ ነዋሪው ወጣት አቤል ባንቀስራ በበኩሉ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በመጠቀም የመራጭነት ካርድ መውሰዱን  ገልፆ፤ ሌሎችም የሱን አርአያነት በመከተል  የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ  ከልምዱ መክረ ሀሳብ መስጠቱን ጠቁሟል ።

በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ልዩ ድጋፍ ለሚሹ አካል ጉዳተኞች የተሻለ ፖሊሲና አቅጣጫ ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተከታተለ መቆየቱንም አመላክቷል ።

"ምርጫ የዜጎችን ተሳትፎና ፍቃድ በማግኘት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመንግስት ስልጣን የሚያዝበት ስርዓት በመሆኑ ይበጀናል ያልነውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል" ያሉት ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ጋሻው መክብብ ናቸው ።

ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ጠንካራና ለሁሉም የምትሆን አገር ለመገንባት መሰረት በመሆኑ በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በቀሪ ቀናትም የምርጫ ካርድ ያላወጣ ነዋሪ በምርጫ ጣቢያዎች ተመዝግቦ ካርዱን በእጁ መያዝ እንዳለበት መክረዋል።

ለጠቅላላ ምርጫው እየተካሄደ ያለው የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም መራዘሙ በርካታ ዜጎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ የዕድሉ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም