ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት …

ከሚያዝያ 5 እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ መመረቅ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ በንፋስ ኃይል አማካኝነት ጨለማን ለመግፈፍ፣ ዐቅምን በለየ የቅድመ ጥናት እና ልዩ ዕቅድ የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫን ዕውን አድርጋለች ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት 100 ሜጋ ዋት ንጹህ የኃይል አቅርቦት በመጨመር ወደ ዘርፈ-ብዙ እና ቀጣይነት ባለው የኃይል መጻዒ ዕጣ ፈንታ ለመገንባት የምናደርገውን ጉዞ ያጠናክረዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ይህም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ አብነት ነው ብለዋል በወቅቱ። በሁሉም ዘርፎች የምናስመዘግበው የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ ተጠናክሮ እየቀጠለ ይበልጥም እየለማ ይሄዳል፤ ከምንጊዜውም በላይ ታላቅ የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ሲሉም አመላክተዋል።

ከኮፕ32 አስተናጋጅነት ጋር በተያያዘ ምክክር መደረጉ

የኮፕ32 አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ዝግጅቷን ቀደም ብላ መጀመሯን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ከብሔራዊ ኮሚቴው ጋር በነበረን ስብሰባ፤ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎችን በመገምገም ክፍተቶችን የመለየት እና ሁሉም ጥረቶቻችን ከሀገራዊ ርዕያችን ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው ተዳሷል ሲሉ ገልጸዋል። ከግምገማ ባሻገር የቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው፤ ትኩረታችን ግልጽ ነው፤ በጠንካራ ትብብር፣ በተዋሃደ ታላቅ ርዕይ እና የጋራ ጽኑ ትጋት ተናበን ይህን ዓለም አቀፍ ሁነት በልኅቀት በማስተናገድ የሀገርን ታላቅነት ዳግም ማሳየት ነው ብለዋል።

የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ለመጡት የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከዚያም በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይትም፤ ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ በቅኝ ያልተገዙ፣ ለአኅጉሩ ነፃነትና አንድነት ድምፅ በመሆን ከጋራ የጽናት ታሪክ የሚመነጭ ጥልቅና ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት አላቸው ያሉት ጠላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬም እንደ ሁሌው ኢትዮጵያ ከሰፊ ገበታዋ ያላትን ታላቅ ዐቅምና ዘላቂ ወዳጅነት አብረዋት ለሚጓዙ ሁሉ ለማካፈል ዝግጁ ናት ብለዋል። ጉብኝቱም በተለያዩ ዘርፎች ያለንን የቆየ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋት ወሳኝ ምዕራፍን ከፍቷል ሲሉ ገልጸዋል።

ከሁለትዮሽ ስብሰባው በመቀጠልም በሁለቱ ሀገራት በኩል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለማሳካት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጡ የመግባቢያ ስምምነቶች እንዲፈረሙ አድርገናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ በፈጣን የለውጥ ጉዞ ያካበተችውን ልምድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል እንዲሁም ከአጋሮቻችን የተለያዩ ዕይታዎችን በመቅሰም ለአኅጉሩ ዕድገት ዘላቂና አፍሪካዊ መፍትሔዎችን በጋራ ለማፍለቅ እንደ ወሳኝ መሠረት ያገለግላሉ ነው ያሉት።

የፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓውሎ ራንገል ጋር ባሳለፍነው ሳምንት በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። በዚሁ ወቅትም፤ የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን እና ቀጣይ ትብብሮችን በምናጠናክርባቸው ቁልፍ መስኮች ላይ መክረናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ማድረጋቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም፤ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ፣ የተሻገረ ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ በበቂ ሁኔታ ዜጎችን ሥራ ለማስያዝ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሚና አይተኬ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።

በዚሁ ወቅትም፤ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሥራ ይፈጥራል፣ ኢኮኖሚ ያሸጋግራል፣ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሻገር እንደ መስፈንጠሪያ ሆኖ ያገለግላል በማለት አብራርተዋል። በእነዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት አንዱ አንጓ ነው በማለት አስረድተዋል።

የብዙ መንግሥታትና የእኛም ትኩረት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ የሆነበት ዋናው ምክንያት፤ ኢንዱስትሪ ማደግ ለሚያስብ ሀገር በጣም ወሳኝ ነገር ስለሆነ ነው ብለዋል። አክለውም፤ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ልብ መሆኑን አስገንዝበዋል። አንድ ሰው ልቡ ካልሠራ ሌላው አካላቱ ጤነኛ ቢሆንም ውጤታማ እንደማይሆን ሁሉ፤ ኢኮኖሚን ኢኮኖሚ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ልብ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የከተማ እና የከተሜነት እሳቤ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬት ያለውን ወሳኝ ሚና አንስተው፤ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሊከናወንና ሊሳካ የሚችለው በጥግግት የሚኖሩ ሰዎች ሲኖሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሕዝብ ጥግግት ለልማት እጅግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልማትንና ብልጽግናን የሚያስብ ማንኛውም መንግሥት ከተማን፣ ከተሜነትን፣ ግብር መክፈልንና አገልግሎት መስጠትን ማዕከሉ ካላደረገ ልማት ሊያመጣ እንደማይችል አብራርተዋል።

ከተማ አያስፈልግኝም፤ የእኔ ትኩረት አርሶ አደር ብቻ ነው የሚል እሳቤ ካለ ልማትን ማሰብ እንደማይቻልም አመላክተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በወሎ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ አሎማ ክላስተር በበጋ መስኖ የለማውን የደረሰ የስንዴ ማሳ በጎበኙበት ወቅት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሀገራችን በምግብ ራሷን ለመቻል የጀመረችው ጉዞ በተግባር ሥር እየሰደደ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የመደመር መንግሥት ለበጋ መስኖና ለስንዴ ምርታማነት የሰጠው ትኩረት የዜጎችን ሕይወት እየቀየረና የሀገርን የምግብ ሉዓላዊነት እያረጋገጠ ይገኛል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተመለከትነው የስንዴ ልማትም የራዕያችንን ውጤት፣ የሐሳባችን መሬት መንካትና ፍሬ የማግኘታችን ተጨባጭ ማሳያ ነው በማለት ገልጸዋል።

እንዲሁም በ "ገበታ ለትውልድ" መርሐ ግብር የተገነባውን የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ሥራ ማስጀመራቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ጸጋን የመለየት፣ የማልማትና ወደ ሀብት የመቀየር ማሳያ እና የወሎ የብልጽግና ተስፋ ነው ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት ከግንባታው ጅማሮ እስከ ፍጻሜው የ"መደመር" ዕሳቤ በተግባር የታየበት፣ የመንግሥት ሐሳብ፣ የባለ ሀብቱ ታታሪነት እና የሕዝቡ ትጋት የተሰባጠረበት ድንቅ ውጤት ነው ሲሉም ገልጸል።

ያየነው ልማት የሰላም ውጤት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ሰላማቸውን አጥብቀው እንዲጠብቁ አደራ በማለት፤ በአንድነት እና በትጋት ከሠራን ይህ ቀጣና የዕድገትና ብልጽግና መዳረሻ መሆኑ አይቀሬ ነው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ የመሠረተ-ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንትን የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ በዚሁ ወቅት መሠረተ-ልማት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ ግብዓቶችን በማመላለስ የኢኮኖሚያችን የደም ሥር፣ የብልጽግናችን መሠረት ነው ብለዋል። በዐውደ ርዕዩ የተመለከትነውም ወሳኝ የልማት ተቋሞቻችን፣ መሠረተ-ልማትን እንደ ሀገር በቅንጅትና በትብብር የመምራት አዲስ የሥራ ባህል እየገነቡ መሆናቸው ነው ሲሉም ገልጸዋል።

መንግሥት በመንገድ፣ በኃይል፣ በመስኖ፣ በባቡርና በዲጂታል መሠረተ-ልማት ዘርፍ ፈጣንና ፍትሐዊ ልማት ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት የሥራ፣ የውጤት እና የተስፋ ዘመን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትናንት የተገነባው ለዛሬ፣ ዛሬ የምንገነባው ደግሞ ለነገው ትውልድ ኩራት እና የብልጽግና ዋስትና ነው ብለዋል።

#ባሳለፍነው_ሳምንት #ኢዜአ   #Ethiopian_News_Agency

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም