የአምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ - ኢዜአ አማርኛ
የአምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ የአንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ስርዓተ ቀብር ዛሬ በእንጦጦ ሀመረ ኖህ ኪዳነ ምህረት አንድነት ገዳም መካነ መቃብር ተፈፅሟል።
አንጋፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጂት ሥነጊዮርጊስ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 29/2018 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አምባሳደር ቆንጂት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በ1950ዎቹ በለጋ እድሜያቸው ተቀላቅለው ከዴስክ ኦፊሰርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ማገልገላቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
አምባሳደር ቆንጂት ከዮዲት እምሩ በመቀጠል በኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሴት አምባሳደርም ነበሩ።
አምባሳደሯ በኦቶዋ፣ካይሮ፣ ቴል አቪቭና ቬይና በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ሰርተዋል።
ከሰኔ 2009 እስከ መስከረም 2011ዓ.ም ደግሞ ኢጋድ በመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ላይም ልዩ አማካሪ ነበሩ።