ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መሳተፍ የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል- የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ የምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በወቅቱ በመውሰድ በምርጫው በንቃት ለመሳተፍ ዕለቱን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም ሲያካሂድ ቆይቷል።

በተጨማሪም ቦርዱ የመራጮችን ምዝገባ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም አራዝሟል።

በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ ድምጽ የሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡

በመሆኑም መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ድምጻቸውን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካካል አቶ ጃፋር መሐመድ እንዳሉት፤ ምርጫ ለአንድ ሀገር ዜጎች በፈቀዱትና በመረጡት መንገድ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር በማድረግ የጋራ ዕጣ ፋንታን በጋራ የሚወስኑበት ትልቅ እድል ነው።

በመሆኑን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸው፤  ይበጀኛል ያሉትን ፓርቲ  ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ በሽር ኢማም በበኩላቸው በሌሎች ሐሳብና ፍላጎት ስር ላለመውደቅ የምርጫ ካርድ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ የመመዝገቢያው ጊዜ አልፎ ከመቆጨት ከመጸጸትን በወቅቱ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በዚህም የራስንና ቀጣይ የአገርን ሰላምና ኢኮኖሚያዊ እደገት ብሎም የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋጋጥ ይቻላል ብለዋል።

አንድ ሀገር ልትመራ የምትችለው የራሷ መሪ ሲኖራት ነው መሪዋን ደግሞ የሚመረጠው በህዝቦቿ ነው በመሆኑም የአገሬን መሪ መምረጥ  ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታዬም ጭምር ያለችን ወይንሸት ፊፋ  ናት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሲያከናውን የነበረው የመራጮች ምዝገባ ማራዘሙ በተለያዩ ምክንያቶች ተመዝግበው ካርድ ለማውጣት ያልተመቻቸው ዜጎች ትልቅ እድል ነው ብላለች።

ምርጫ የወደፊት ህልሜን ያሳካልኛል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ የሚረዳኝ  አጋጣሚ በመሆኑ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለው ያለን ደግሞ ወጣት መሐመድ ዘይኔ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም