በክልሉ በማህበረሰቡ ተሳትፎ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በማህበረሰቡ ተሳትፎ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ቡኢ፤ ሚያዚያ 10/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማህበረሰቡ ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በህብረተሰብና በባለሀብቱ ተሳትፎ ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዲስ መልክ ተገንብቶ የተጠናቀቀውን የሶዶ ቡኢ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።
የትምህርት ዘርፉን መደገፍ የዕድገት ጉዞን ለማፋጠን ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በሥነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።
መንግሥት በትምህርት ዘርፉ የተስተዋለውን ስብራት ለመጠገን ማህበረሰቡን ያሳተፉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በባለሀብቱና በማህበረሰቡ ተሳትፎ እንደ አዲስ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው የሶዶ ቡኢ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአካባቢው ባለሀብቶች የትምህርት ዘርፉን ለማጠናከር የጀመሩትን አስተዋጽኦ በሌሎች የልማት ሥራዎችም ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው ህብረተሰቡ ለአካባቢው ፈጣን እድገት መረጋገጥ በተለያየ መንገድ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በማህበረሰቡ ተሳትፎ ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በአዲስ መልክ ተገንብቶ ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው የሶዶ ቡኢ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእውቀት የታነጹ ዜጎችን በማፍራት በኩ አስተዋጾው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ተሞክሮውን በሌሎች የዞኑ መዋቅሮች በማስፋት በዘርፉ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
ለትምህርት ቤቱን መልሶ ግንባታ ጥሪ ሲቀርብ ባለሀብቶችን በማስተባበር ሀላፊነታቸውን መወጣታችውን የገለጹት ደግሞ ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም ናቸው።
ትምህርት ቤቱ ከገጠመው ችግር ወጥቶ የመማር ማስተማር ስራን በተሻለ ለማከናውን በሚያስችል መልኩ ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱን ጠቁመዋል።
ትምህርት ቤቱ በአዲስ መልክ መልሶ መገንባቱ ምቹ የመማሪያ አካባቢን ፈጥሯል ያለችው ደግሞ በትምህርት ቤቱ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ቃልኪዳን መርሻ ናት፡፡
ትምህርት ቤቱ ከዚህ ቀደም የነበረበትን የቤተ ሙከራ እና የቤተ መጻህፍት አቅርቦት ችግር ከመፍታት ባለፈ የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችለው መሆኑን ገልጻለች።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የምስራቅ ጉራጌ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶች፣ ነዋሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡