ወጣቶች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በቀሪ ቀናት በመውሰድ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የክልሎች የወጣቶች ቢሮ ሀላፊዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
ቦርዱ ለአንድ ወር የሚቆየውን የመራጮችን ምዝገባ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም አራዝሞታል።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ ድምጽ የሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡
በመሆኑም መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
ከክልሎች የተወጣጡ የወጣቶች ቢሮ ሀላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምርጫ በሀገር ጉዳይ የመወሰን እድል ስለሆነ ወጣቶች ይህን ተረድተው በቀሪ ቀናት ካርድ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
ምርጫ ለሀገር እድገት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እጅግ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ዜጎች በየጊዜው በምርጫ አማካኝነት መሪዎቻቸውን በመምረጥ፤ ይህም ይጠቅመናል ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሳል ለሚሉት እጩ የመንግስትን ስልጣን በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ በአደራ የሚሰጡበት ነው።
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ በሚገኘው የመራጮች ምዝገባ በመሳተፍ ካርድ ያልወሰዱ ወጣቶች ተመዝግበው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ሱልጣን አሊ እንደገለጸው፤ በክልሉ ወጣቶች በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ በምርጫ ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ የማንቃት ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ብሏል።
ምርጫው በሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሂደት እንዲጠናቀቅ ወጣቶች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ በንቃት በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ አለባቸው ሲልም ገልጿል።
በሲዳማ ክልል የወጣቶች ማህበር አባል በቃሉ መሰረት በበኩሉ፤ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት ከምርጫ ምዝገባ ጀምሮ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከሲቪክ ማህበራትና ሌሎች አጋሮች ጋር እየተሰራ ነው።
ምርጫ በሀገር ጉዳይ ላይ የመሳተፍ ብቻ ሳይሆን፤ የመወሰንም እድል በመሆኑ ወጣቶች ከምዝገባ ጀምሮ በንቃት ሊሳተፉ ነው ሲልም ተናግሯል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች ጉዳይና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ኮሚሽነር ወጣት ማርቆስ ማቲዎስ፤ ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጭነት፣ በታዛቢነት በእጩ ተወዳዳሪነት እንዲሳተፉ በተከናወኑ ስራዎች ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የገለጸው።
በክልሉ ወጣቶች ከመራጭነት ባለፈ በታዛቢነትና በእጩ ተወዳዳሪነት ተሳትፎ እያደረጉ መምጣታቸውን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እስከ ሚያዝያ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 46 ሚሊዮን 736 ሺህ 895 ዜጎች ለመራጭነት መመዝገባቸውን አስታውቋል።