ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭና ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁባቸው መድረኮች መመቻቸት የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመወሰን ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭና ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁባቸው መድረኮች መመቻቸት የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመወሰን ያስችላል
ሚዛን አማን፣ ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ) -የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጭና ፕሮግራማቸውን የሚያስተዋውቁባቸው መድረኮች መመቻቸት የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ ለመወሰን እንደሚያስችላቸው የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየት ሰጪዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ተመዝግበው የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች በቀሪ ጥቂት ቀናት በመመዝገብ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን መጠቀም እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ የተለያዩ የጊዜ ሰሌዳዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።
ከዚህ ውስጥም ለመራጭነት የሚያበቃ የምርጫ ካርድ መውሰጃ ጊዜ ሰሌዳ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናቶች ቀርተውታል ።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ለሀገር የሚጠቅም ፓርቲን ለይቶ ድምጻቸውን ለመስጠት ፓርቲዎች የሚያደርጓቸውን ክርክርች እና ያሏቸውን ፕሮግራሞቻቸውን በመከታተል ላይ ናቸው።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ማለቶ ታከለ እንደሚሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን የፐሊሲ አማራጮችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በመከታተል በምርጫው ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ዝግጅት እያደረጉ ነው ።
በፌዴራል ደረጃ በቴሌቪዥን ከሚደረግ የምርጫ ማኒፌስቶ ማስተዋወቅ መርሐ ግብር ባሻገር በክልል ደረጃም መሰል ትግባራት መከናወናቸው ለመራጩ ሕዝብ በቂ ግንዛቤ እየተፈጠረለት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በራስ ፍላጎት የሚያስተዳድረንን መንግስት የምንመርጥበት በመሆኑ እስካሁን የመራጭነት ካርድ ሳይወስዱ የዘገዩ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም በቀሪ ጊዜያት ካርድ ማውጣት ይገባቸዋል ሲሉም መክረዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ መምህርት አልማዝ ዓለምገና፤ በመገናኛ ብዙሃን የሚካሔዱ የፓርቲዎች ክርክሮችና የፕሮግራም ማስተዋወቂ መድረኮች በምርጫው ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ ሀሳብ ያለውን የተሻለ ፓርቲን ወደ ስልጣን ለማምጣት ግንዛቤ እየፈጠሩላቸው መሆኑን ገልጸዋል
ነገ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት አንድ ድምጽ ወሳኝ በመሆኑ በዴሞክራሲ ግንባታ፣ በልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በማኅበራዊ አገልግሎቶች የተሻለ ሀሳብ ያለውን ፓርቲ በነጻነት ለመምረጥ ተዘጋጅቺያለሁ ሲሉ ገልጸዋል።
ወቅቱ በሀገርና በፖለቲካ እሳቤዎች ላይ የሕዝብ ንቃተ ሕሊና የጨመረበት በመሆኑ ሰላማዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት።
ለአካባቢያችን ለውጥና ዕድገት ብሎም ለሀገር አንድነት መጠናከር የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫው የሚሳተፉት ወጣት ታምራት አድማሱ እና አሻግሬ መቹል ናቸው።
ለመምረጥ ከመዘጋጀት ባሻገር ለምርጫው ሰላማዊነትና መረጋጋት እንደ ወጣት ባለንበት አካባቢ ሚናችንን እንወጣለን ሲሉም አክለዋል።