ቀጥታ፡

በክልሉ የማይበገር ዘላቂ የጤና ስርአት በመገንባት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

ጎንደር ፤ሚያዝያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የማይበገር  ዘላቂ የጤና ስርአት  በመገንባት  የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። 

በጎንደር ከተማ የሚገኘው  የጠዳ  ከፍተኛ ትምህርት ጤና ሳይንስ ኮሌጅ  በጤናው ዘርፍ በመካከለኛ ደረጃ ሙያተኝነት  ያሰለጠናቸውን 445 ባለሙያዎችን ዛሬ አስመርቋል።  

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ አብድልከሪም መንግስቱ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግስት የጤናው ዘርፍ ልማት ለማፋጠን እየሰራ ነው።


 

በዚህም ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራት ተደራሽነትና ፍትሀዊነት ለማረጋገጥ  የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ነው የገለፁት። 

በአሁኑ ወቅት ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን በማረጋገጥ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘላቂነት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ በኩል የጤና ሙያተኞች  አስተዋጽኦ  ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው ብለዋል።

''የዛሬ ተመራቂዎች ሙያችሁን በርህራሄ፣ በታማኝነትና በከፍተኛ የሙያ ስነ- ምግባር በመፈጸም  ለህዝብ የገባችሁትን ቃለ መሀላ በተግባር ልታረጋግጡ ይገባል'' ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው ፤የህክምና ሙያ ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት የመታደግ ታላቅ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።  


 

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ስራው ባሻገር በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለከተማው የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ሰፊ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።   

የኮሌጁ ዲን አቶ ዘመነ ሀብቱ  በበኩላቸው፤  ኮሌጁ   በዛሬው እለት ያስመረቃቸው 445 የመካከለኛ ደረጃ የጤና ባለሙያዎች  መሆናቸውን ነው የተናገሩት።  

ኮሌጁ በፋርማሲ፣ በላቦራቶሪ፣ በጤና መረጃ ስርአትና በጤና ኤክስቴንሽን  የትምህርት ዘርፎች ካሰለጠናቸው የዛሬ ተመራቂዎች መካከልም 439  ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።    

ተመራቂዎች በቀሰሙት የህክምና ሙያ በላቀ ብቃት፣  ስነ-ምግባርና ሰብአዊ ርህራሄ ህዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።   

በፋርማሲ የትምህርት ክፍል 21 A በማምጣት በከፍተኛ ማእረግ የዋንጫና የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው እያሱ አሰፋ ፤ በ ቴክኖሎጅ በመታገዝ  ሙሉ ጊዜውን ለጥናትና  አውሎ ውጤታማ መሆን እንደቻለ ተናግሯል።

ከፋርማሲ የትምህርት ክፍል ሶስት ነጥብ 97 በማምጣት   በከፍተኛ ማእረግ የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነችው አማረች መልኬ፤  በራሴ ጥረትና በወላጆቼ ያልተቆጠበ ድጋፍ ስኬታማ ለመሆን በቅቻለሁ ብላለች። 

በቀሰመችው ሙያ ሀገርና ህዝቧን በታማኝነት በማገልገል  ሙያዊ ኃላፊነቷን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑዋን ነው የተናገረችው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም