ቀጥታ፡

በእግር ኳስ የታዳጊ ወጣቶችን አቅም በማጎልበት ብቁና ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ሥራን ማጠናከር ይገባል

ሐረር፤ ሚያዚያ 10/2018 (ኢዜአ)፦ በእግር ኳስ የታዳጊ ወጣቶችን አቅም በማጎልበት ብቁና ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ሥራን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናገሩ።

የሐረሪ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን አደረጃጀትን በአዲስ መልክ ለማዋቀር አስቸኳይ ጉባዔ ዛሬ ተካሂዷል።

በተካሄደው ጉባዔ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መተዳደርያና የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንቦች ላይ ውይይት ከተካሄደ በኋል በሙሉ ድምጽ ጸድቀዋል።

እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተመረጡ ሲሆን በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ላይ በሚያጋጥሙና በቀጣይም ስጋት ይሆናሉ በተባሉ ጉዳይዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በጉባዔው ላይ የተገኙት የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የእግር ኳስ ስፖርት በህብረትና በአንድነት መቆምን የሚጠይቅ በመሆኑ ተቀናጅቶ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ብለዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎችም በአካባቢው ያሉ አቅሞችን ለይተው በመጠቀም ብቁና ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ላይ ተግተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እንደ ጸጋ በመቀበልና ተጋፍጦ በመስራት ብቁና ተተኪ ወጣት ስፖርተኞችን ማፍራት  ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለዚህም በክልሉ የታዳጊ ወጣቶችን አቅም በማጎልበትና አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት በብሔራዊ ቡድን ግንባታ ላይ ክልሉ የበኩሉን ማበርከት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወጣቶች ልማት ላይ የሚያከናውነውን አመርቂ ተግባር ተከትሎ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የሐረሪ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ መሀመድ ያህያ በበኩላቸው ጉባዔው የክልሉን እግር ኳስ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረው ነው ብለዋል።

በክልሉ እግር ኳስ ልማት ላይ የተስተዋሉ ውስንነቶችን በመፍታት ብቁና ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ተግባርን የማስቀጠል ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙራድ አብዲ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት የማጠናከር፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የማጎልበትና ሌሎች የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም