ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ370 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል

ደብረ ማርቆስ፤ ሚያዚያ 10/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን ባለፉት 9 ወራት ከ370 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ  ውሃ እና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፍሬው ካሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት 499 አነስተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ከዚህ ውስጥም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ370 በላይ የሚሆኑ አነስተኛ የንጹሕ ውሃ ተቋማት ግንባታን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ መቻሉንም ነው የገለጹት።

ቀሪዎቹን ደግሞ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ለውሃ ተቋማቱ ግንባታ ከዋለው 150 ሚሊዮን ብር ውስጥ 50 ሚሊዮን ብሩ ከማሕበረሰቡ ቀሪው ደግሞ ከመንግስት የተገኘ መሆኑንም አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ የሚገነቡት የውሃ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ከ92 ሺህ በላይ የሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የሚገነቡት የውሃ ተቋማት ሲጠናቀቁ የዞኑን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት ከ48 ነጥብ ሰባት በመቶ ወደ 52 በመቶ ለማሳደግ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም